የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

AMN – ኅዳር 12/2017 ዓ.ም

በዜጎች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን የ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) የተቋሙን አሠራር በማዘመንና የሰው ኃይሉን በማጠናከር ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ግልፅ የአሠራር ሥርዓትን በመዘርጋትና ጥፋተኛ ሰዎችን ተጠያቂ በማድረግ እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብልሹ አሠራርንና ሙስናን በዘላቂነት መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሕጋዊ መንገድ ፓስፖርት የሚያገኙ ከሆነ የውጭ አገር ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለምን በሕገ ወጥ መንገድ ፓስፖርት ለማግኘት ይፈልጋሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተቋሙ ራሱን መፈተሽ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት፣ በኅብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በተቋሙ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ብቃትና ሥነ-ምግባር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የድንበር ቁጥጥር ማጠናከር እና ከፓስፖርት ዋጋ ጭማሪ ጋር በተገናኘ የግንዛቤ ማስጨባጫ ትምህርት መስጠት እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል።

የአሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት ማብራሪያ፣ በተቋሙ ውስጥ የነበረውን ብልሹ አሠራርና ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቴክኖሎጂን በመጠቀም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በድንበር አካባቢ ያለውን ቁጥጥር ለማጠናከር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተቋሙ ለፓስፖርት ከሚያወጣው ወጪና ከሌሎች አገሮች የፓስፖርት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ተቋሙ ለፓስፖርት የሚያስከፍለው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ፓስፖርት ማግኘት እንዲችል በአዲስ አበባ አራት ቅርንጫፎችንና ከአዲስ አበባ ውጭ ማዕከላዊ በሆኑ ቦታዎች አሥር ቅርንጫፎች ተከፍተው ለኅብረተሰቡ በቅርብ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አብራርተዋል።

ኅብረተሰቡ ስለ ተቋሙ አጠቃላይ አሠራርና ፓስፖርቱን በየአካባቢው ባሉ ቅርንጫዎች መውሰድ እየቻለ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ እየተጉላላ በመሆኑ ከመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት ገዝተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review