AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
ዛሬ ጠዋት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያና የጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም ተሳታፊዎች በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አውደ ርዕይ ማዕከልን መጎብኘታቸውን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ ባላት የተለያየ መልከዓ ምድር ምቹ የአየር ንብረት ብዝሃ-ምርቶችን አምርታ ለዓለም የማቅረብ ዕምቅ አቅም አላት ብለዋል፡፡
ማዕድንን እንደማሳያ ብንወስድ ባለፉት ስድስት ወራት ከወርቅ ብቻ 1 ነጥብ 36 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተናል ብለዋል፡፡
አቅማችንን አጎልብተን ወደ ገቢራዊ ውጤት መቀየርና በልኩ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ አኛም ይህን ታሳቢ በማድረግ በጃፓን ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለመላክ በሚያስችል መልኩ ለልዑካን ቡድኑ ግንዛቤ ሰተናል ብለዋል፡፡
የቡና፣ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ሰብሎች፣ ቅመማቅመም፣ አትክልትና ፍርፍሬ፣ ማዕድንና ሌሎች ምርቶቻችንን በጥራት አምርተን በውጪ ንግድ የዓለም ገበያ ያለን ድርሻ እያሻሻልን ከሄድን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ በብዙ እጥፍ ይጨምራል ሲሉም አመልክተዋል፡፡