የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልዕልና በአጠረ ጊዜ እውን ለማድረግ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልዕልና በአጠረ ጊዜ እውን ለማድረግ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN ሰኔ 8/2017

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልዕልና በአጠረ ጊዜ እውን ለማድረግ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ “በቀል በቀለኛውን ያጠፋል” በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሃፍ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ፓስተር ጻድቁ አብዶ በዘመናቸው ያካበቱትን እውቀት ለትውልድ በሚጠቅም መልኩ ቀምረው ለንባብ በማቅረባቸው አመስግነዋል።

በቀለኝነት፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ጸር መሆኑን ገልጸው፤ የየትኛውም ሃይማኖት የአስተምህሮ አለመሆኑን ተናግረዋል።

አገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የአገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ ያላት መሆኑን ያወሱት ከንቲባ አዳነች፤ በተለያዩ ዘርፎች ግን የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተለይ በኢኮኖሚ ሌሎች አገራት የደረሱበት ደረጃ መድረስ ያልቻለችበት አንዱ ምክንያት የእርስ በእርስ መገፋፋት መሆኑን አንስተዋል።

የአገርን ሁለንተናዊ ልዕልና በአጠረ ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ በይቅርታ አብሮነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘ ካቶሊካውያን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መፅሀፉ ለትውልዱ መልካም ስብዕና ይዞ ለጋራ ዓላማ በጋራ እንዲቆም እውቀት ያስጨብጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መጽሃፉ በተለይ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እያከናወነ ላለው ተግባር ግብዓት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በቀል በግለሰብ እና በትውልድ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ መጽሃፉ አዲሱን ትውልድ የሚቀርጽ ነው ብለዋል፡፡

ስለዚህ አሁን ላለነውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ ሲባል ይቅር መባባል ይገባናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንትና የመጽሀፉ ጸሀፊ ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው፤ የመጽሃፉ ዋና ዓላማ ሁሉም ራሱን መርምሮ ከክፋት እንዲርቅና መልካሙን እንዲከተል ለማድረግ መሆኑን መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

ፍርድን ለፈጣሪ በመተው ራሱን ለይቅርታ እና ለወንድማማችነት ማዘጋጀት እንደሚገባም አመልክተዋል።

መጽሃፉ ሶስት ምዕራፎችና 150 ገጾች አሉት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review