AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ የተጀመሩ የልማት እና የዲሞክራሲ ስራዎችን እንደ እድል ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገለጹ፡፡
አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ኢብራሂም በማብራሪያቸው ከዚህ ቀደም የተዛቡ ትርክቶች ለችግሮች መነሻ የሆኑ እና ችግሮችን ሲፈጥሩ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸው ይህን ከማስተካከል አንጻር የብልጽግና ፓርቲ ከመጀመሪያው ታሪካዊዉ ጉባኤው አንስቶ በርካታ ስራዎች መስራቱን ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና የሚያምነው በውይይት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ ትርክት መገንባት አለብን ተብሎ ሲሰራ መቆየቱንም አውስተዋል፡፡
በመሆኑም ከለውጡ ወዲህ የሚያኮሩ ድሎች መመዝገባቸውን አውስተው ከእነዚህ ድሎች መካከል የህዳሴው ግድብን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የምትታወቀው በልመና እና በተረጂነት ቢሆንም አሁን ላይ በስንዴ ምርት ላይ በተሰራው ስራ ትልቅ የታሪክ እጥፋት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ስንዴን በማምረት ለስንዴ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችው ስራ ከፍተኛ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በቀጣይ ህብረብሄራዊነታችንን የሚያጠናክሩ ስራዎች በስፋት መሰራት አለባቸው ያሉት ኃላፊው ልዩነቶቻችን ውበት እንጂ የግጭት ምንጭ ሊሆኑ አይገባም ብለዋል፡፡
በዚህም አሰባሳቢ እና ገንቢ የሆኑ ታሪኮቻችን ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
እንደ ብልጽግና በዋናነት የምንገነባው ብሄራዊ ትርክትን ነው ያሉት ኃላፊው ከዚህ ቀደም ይዘናቸው የመጣናቸውን የተዛቡ ትርክቶች ማረም አለብን ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ይሁን እና ከዚህ ቀደም የነበሩ በጎ ስራዎችን ደግሞ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ፤ የሌማት ትሩፋት፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና የግብርና ስራዎችን እንደ ትልቅ እድል ተጠቅመን ልንሰራባቸው የሚገቡ ስራዎች ናቸውም ሲሉም አክለዋል፡፡
ቀጣይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ እነዚህን ስራዎች እንደ እድል መጠቀም ይገባልም ብለዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ