የኢትዮጵያን ተመራጭ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማስፋት ሁሉም ዜጋ አምባሳደር መሆን ይገባዋል – አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

AMN – ታህሳስ 7/2017 ዓም

የኢትዮጵያን ተመራጭ አለም አቀፋዊና አህጉራዊ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማስፋት ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ አምባሳደር መሆን እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለፁ።

ለ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና ለ46ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ቅድመ ዝግጅት የበጎ ፈቃድ ፕሮቶኮሎችና የመሪ ባልደረቦች ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያ 38ኛውን የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያካሄደች ነው ብለዋል።

ጉባዔው ኢትዮጵያን ይበልጥ ከማስተዋወቅና ገፅታን ከመገንባት ባለፈ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የምናጠናክርበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ተመራጭ አለም አቀፋዊና አህጉራዊ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማስፋት ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለጉባዔው ይህን የሚመጥን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 የሚካሔድ ሲሆን የካቲት 8 እና 9 ቀን ደግሞ 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review