AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ የሚሳካው በተቋሞቻችን ጥንካሬ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላትን የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
ግምገማውን አስመልክተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስሰር ገፃቸው ባስፈሩት መልዕክት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት መንግሥት ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ በልዩ ትኩረት ሠርቷል ብለዋል።
በተለይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ራሳቸውን በአግባቡ በማደራጀት ለሀገር ግንባታ የሚቆጠር አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ እንደሆኑም አንስተዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ መስኮች ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች የተቋሞቻችን የመፈጸም አቅም ማሳያ ናቸውም ብለዋል።
በቀጣይም ተቋማቱ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት አገልግሎት አሰጣጣችንን ማዘመን፣ ወጪ ቆጣቢ አሰራርን መከተል፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና በተሰጠን ተልዕኮ የምንፈጥረውን በጎ ተፅዕኖ እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን በቀጣይነት እየገመገሙ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉም አክለዋል፡፡