የኢትዮጵያውያኑ ሀጃጆች ‘በምህረት ተራራው’

You are currently viewing የኢትዮጵያውያኑ ሀጃጆች ‘በምህረት ተራራው’

መካ፣ ሚናና አረፋ የሚሰኙ ስፍራዎች  አቅሙ የፈቀደለት አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲሄድ የሚገደድባቸው ቅዱስ ስፍራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ታዲያ የኢኮኖሚ አቅም ብቻ በቂ አይደለም፡፡

እጅግ አስቸጋሪና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ፣ አናት የሚበሳውን ፀሐይ፣ ከባዱን ሀሩር ተቋቁሞ ማለፍም የግድ ነው፡፡ መዳረሻው ደግሞ ቅዱሱ ስፍራ (Mount of Mercy) “አረቦች ጀበል አል ራህማ (የምህረት ተራራ)” በማለት የሚጠሩት የአረፋ ተራራ ነው፡፡

የእስልምና እምነት መነሻ የሆነችውን መካን መጎብኘት የሙስሊም ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ በሙስሊሞች ላይ የተጣለው መካን የመጎብኘት ግዴታ የተግባሩን ትልቅነት በሚያሳይ “ሀጅ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ሀጅ ማድረግ ደግሞ የአንሷር መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሀመድ ሳሊህ እንደሚሉት ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት መካከል አንዱ ነውና ማንኛውም አቅም ያለው ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ መፈፀም ይኖርበታል፡፡

በእስልምና እምነት አስተምህሮ ሀጅ የዕድሜ ልክ ኢባዳ (ፈጣሪ የሚወደው ስራ) ነው ይላሉ የዕምነቱ ተከታዮች፡፡ በእርግጥ ሀጅ በምዕመናኑ ዘንድ ግዴታ የማሟላት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በፍቅር የሚያደርጉት፣ አቅሙ የሌላቸው ደግሞ ሀጅ ሳያደርጉ እንዳይሞቱ ለፈጣሪ ፀሎት የሚያደርሱበት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ከመካ በስተምሥራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን ቅዱስ ተራራ መመልከትና ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶችን በዚያው መፈጸም እንደሚገባም የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ያዛል።

በሀጅ ወቅት አማኙ ምን እንደሚፈጽም የሚያስረዱት አየር ጤና አካባቢ የአንሷር መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሀመድ ሳሊህ ጀማል ሀጅ፣ የሚያደርግ ሰው ከያለበት ተሰባስቦ መካ ያርፋል፡፡ ስንቁን አዘጋጅቶ ጉዞውን ይጀመራል፡፡ ሀጅ እስከሚያልቅ ዝክር፣ ውዳሴ፣ ቁርአን መቅራት ሰላትና ዱአ በማድረግ ፈጣሪውን ያመሰግናል፡፡

ይህም በእስልምና ሐይማኖት የመጨረሻው መልዕክተኛ ናቸው ተብለው የሚታመኑት ነቢዩ መሀመድ(ሰ ዐ. ወ) የመጨረሻ ጸሎት እስካደረጉበት ቦታ አረፋ ድረስ ይቀጥላል። ሀጃጆችም በሀጅ ጸሎታቸው የነቢዩን ተምሳሌት በመከተል በአረፋት ኮረብታ ዙሪያ በነሚራ መስጅድና በምህረት ተራራ “ጀበል አረፋ” ላይ ሙሉ ቀን ጸሎት ሲያደርጉ ይውላሉ፡፡

የአረፋ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ቋንቋ ሳይገድባቸው፣ የቆዳ ቀለም ሳይለያቸው፣ ስፍራና ማንነት ሳያግዳቸው በአንድ አይነት አለባበስ በአንድነት በቅድስቲቱ ምድር መካ በመሰባሰብ ጥያቄያቸውን ለፈጣሪ የሚያቀርቡበትም ስለመሆኑም ሼህ ሙሀመድ ሳሊህ ያስረዳሉ።

ሼህ ሙሀመድ እንደሚሉት የአረፋ በዓል በሁለት አይነት መልኩ ይከበራል፣ አንደኛው ሃይማኖታዊ መስፈርቶችን ጠብቆ ወደ መካ በመሄድ የሚደረግ የጸሎት ሥነሥርዓት ሲሆን የሀጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ዋንኛው የአረፋ ተራራን መውጣት ሌላኛው ነው። የጤናና የገንዘብ አቅማቸው የፈቀደላቸው የሀይማኖቱ ተከታዮች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ቅድስቲቱን ምድር መካን በሀጅ ሥርዓት መካፈል ይጠበቅባቸዋል።

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ከአምስቱ የእስልምና መሰረቶች አንዱ የሆነው የሀጅ ሥነ-ሥርዓት የሚከወንበት ታላቅ በዓል ነው የሚሉት የአብደላ ኢብኑ አባስ መስጂድ ኢማም ሸይኽ ሙሀመድ ሲራጅ የሀጅ  ዋጅብ (ግዴታዎች) ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያብራራሉ፡፡ ፀሐይ እስክትጠልቅ አረፋ ላይ መቆም፣ የአያመል ተሽሪቅ ሌሊቶችን ሚና ማደር፣ ጀመራት ላይ ጠጠር መወርወር፣ ፀጉርን መላጨት ወይንም ማሳጠር፣ የመሰናበቻ ጠዋፍ ማድረግ ከግዴታዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የበዓሉ ስም የእስልምና ትልቅ ቦታ ካለው እና በመካ አካባቢ ከሚገኘው የአረፋ ተራራ ጋር የተሳሰረ መሆኑን የሚያነሱት ኢማሙ፣ ህዝበ ሙስሊሙ ለ9 ቀናት ከበዓሉ አስቀድሞ እንደሚጾም ይናገራሉ፡፡ በአረፋ ወቅት ከሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱ የሀጅ ሥነ-ሥርዓት፣ ካእባን መዘየር እና ጠዋፍ መጠወፍ እንዲሁም የእርድ ሥነ-ሥርዓት መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

እንደዚሁም የአላህን ቤት ይዞራሉ፣ ጠጠር ይወረውራሉ፣ ሌሎችም ተምሳሌታዊ ተግባራትን ያከናውናሉ። በምድረ በዳ ላይ ለእስማኤል ከፈለቀለት ዘምዘም ውሃ ይጎነጫሉ። ሀጃጆች በቆይታቸው እኩልነታቸውን እንዲያንፀባርቅ “ኢህራም” የሚባለውን ነጭ ልብስ እንዲለብሱ ይደረጋል፡፡ ይህ ነጭ ልብስ እኩልነትን ብቻ ሳይሆን ሰዎች በፈጣሪ ፊት ሲቀርቡ ምንም ሳይዙ መሆኑንም የሚያሳይ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያውያን የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም በስፍራው ተገኝተው በዓመታዊው የሀጅ ጉዞ ፍጻሜው የአላህን ይቅርታ፣ ሰላምና ምህረት ለማግኘት እጃቸውን ዘርግተው ይለምናሉ፡፡ ሀጃጆች “ጥሪህን ተቀብለን መጥተናል” የሚለው ልዩ የሀጀ ጸሎት በህብረት ይዘምራሉ፡፡

መካ ከደረሱም በኋላ ንጋት (የፈጅር ጸሎት) ድረስ ሚና ላይ ጸሎት ከውነው ወደ አረፋ ያቀናሉ፡፡ ወግፍ አረፋ በሚባለው የአረፋ ተራራና ኮረብቶች ተሰብስበው ፊታቸውን ወደ ፈጣሪ በማቅናት በጥልቅ ስሜት ጸሎተ ምህላ ያደርጋሉ፡፡ ነጭ ካባ ለብሰው ነቢዩ መሐመድ የመጨረሻ ስብከታቸውን ያደረጉበትን የአረፋትን ሜዳ የሚቆጣጠረውን ዓለታማውን የምህረት ተራራ በመውጣት በዓሉን ማክበርም ለዓመታት ሲከወን የቆየ አይማኖታዊ ኢባዳ ነው፡፡

እንደ ሼህ ሙሀመድ አስተያየት እንደ ዛሬው በአውሮፕላን በረው ወይም ዱሩን በመኪና አቋርጠው፣ ባህሩን በመርከብ ገስግሰው በሰዓታት በሚደርሱበት የሚከውኑት ጉዞ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በነበረው የመጓጓዣ ዘዴ ተጠቅመው ነበር የእምነቱ ተከታዮች ከያሉበት መካ ላይ የሚሰባሰቡት፡፡ ግመልና ፈረሶች ብቸኛ መጓጓዣ በነበሩበት በዚያ ዘመን የነበሩ እንኳ መካ እስኪደርሱ ወራትን ፈጅተው ከአድካሚ ጉዞ በኋላ ነበር መካ የሚደርሱት፡፡

በእግርና በግመል ተጭነው መካ የገቡ ኢትዮጵያውያንም እንዳሉ የሚነገር ሲሆን ከዚህም ባሻገር ሀጅ የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ነገር ግን አቅሙም ጉልበቱም የሌላቸው ኢትዮጵያዊ ዓሊሞች ባልታወቀ ተዓምር መካ ደርሰው እንደታዩም በታሪክ ይነገራል፡፡

ሀጃጆች በከፍተኛው ሙቀት ረዥም ርቀት በእግራቸው ይጓዛሉ። በበጋ ወቅት አንድ ሀጅ በቀን ወደ 15 ኪሎ ሜትር በእግር ሊጓዝ ይችላል። ይህም ለከፍተኛ ሙቀት፣ ድካም እና ለውሃ እጥረት ያጋልጣቸዋል። ለተጓዦች በተዘጋጁ መጠለያዎች ውስጥ እስከ 51 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርስ ሙቀት ውስጥ መገኘት ግድ ይላል፡፡ ሀጃጆች ብዙም ባለመዱት ሙቀት፣ በአድካሚ የእግር ጉዞ፣ መተፋፈግና በላብ መዘፈቅ ባስ ሲልም በሀጅ ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ የሚከሰት ሞት አዲስ አይደለም። እዚህ ጋር ከአመት በፊት የተከሰተን ሁነት አሰታውሰን እንለፍ፡፡

በዓለማችን በርካታ ሕዝብ ከሚታደምባቸው ሁነቶች ውስጥ አንዱ በሆነው የሀጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይጓዛሉ። ከአንድ ዓመት በፊት የሀጅ ጉዞ የተጠናቀቀው ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ነበር። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ይፋ ባደረገው አሃዝ የ10 ሀገራት ዜግነት ያላቸው ከ1 ሺህ በላይ ሀጃጆች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል። የአብዛኞቹ ሞት ምክንያትም ከከፍተኛ ሙቀት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

ሀጅ ጉዞን በተመለከተ ከወደ ኢንዶነዢያ የተሰማውን እጅግ አስገራሚ ተግባር አቅርበን ጉዳያችንን ወደመቋጨቱ እንለፍ፡፡ በፅዳት ሰራተኝነት የሚተዳደሩ ባልና ሚስቶች ሀጅ ሊያደርጉ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀኑት ለ40 ዓመታት በመቆጠብ ነበር።

ሀጅ ለማድረግ ሳዑዲ አረቢያ የገቡት ኢንዶነዢያዊ ባልና ሚስቶች እንደገለፁት ሀጅ ለማድረግ በህይወት ዘመናቸው በሙሉ ሲመኙት የነበረና ለዚያም ለሀጅ ብቻ በሚል ለ40 ዓመታት ሲቆጠቡ እንደነበር በማንሳት “አላህ በዚህ ዓመት እንድንሄድ ስላደረገን አልሀምዱሊላህ” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሀጃጆችን በመላክ ኢንዶኖዢያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትመደብ ሲሆን ዘንድሮም ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ሀጃጆች ወደ ሳዑዲ አረብያ እንደሚያቀኑ ተገልጿል።

በአጠቃላይ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው። በዓሉ በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት ነብዩ ኢብራሂም የአላህ ትዕዛዝን ለመፈጸም በፍጹም ትህትና እና ታዛዥነት ልጃቸው እስማኤልን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት ስለመሆኑም የዕምነቱ አስተምሮ ይነግረናል፡፡ በበዓሉም ወቅት የሀጅ ስነ ስርዓት የሚከናወን ሲሆነ በየዓመቱም እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሙስሊም ከመላው ዓለም ወደ ሳውዲ አረቢያ በማቅናት ሥርዓቱን ይታደማል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም የዚሁ አካል ናቸው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review