AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን እንዲራዘም የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል።
አባላቱ ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ለሀገራዊ ምክክሩ የሚያግዙ የአጀንዳ ማሰባሰብን ጨምሮ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልፀው፤ በዚህም ኮሚሽኑ ሊመሰገን እንደሚገባ አንስተዋል።
ኮሚሽኑ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በርካታ ስኬታማ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም ዋና ዋና እና አንኳር ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው የስራ ዘመኑ እንዲራዘምና ለሀገር እና ለህዝብ እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን ስራዎች ኮሚሽኑ እንዲያጠናቅቅም ነው ከምክር ቤት አባላት በአፅንኦት የተጠየቀው።
በሀገራችን የተጀመረው የምክክር ሂደት በታሪክ የመጀመሪያውና የማይገኝ ዕድል ነው ያሉት የምክር ቤት አባላቱ፤ ኮሚሽኑ የጀመራቸው ስራዎች ለበርካታ ዘመናት የህዝብ ጥያቄ የነበሩ ሀሳቦች ወደ ምክክር ቀርበውና ህዝብ ተወያይቶባቸው መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በአስር ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እስካሁን በሰራቸው ስራዎች ህዝቡ ተስፋ እንደጫረበትም አንስተዋል።
በቀጣይም ግጭት ባለባቸው በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች እንዲሁም በትግራይ ክልል በኮሚሽኑ ያልተሰሩ ስራዎች እንዲጠናቀቁ አባላቱ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይም በሀሳብ ልዩነት ጠመንጃ ይዘው ወደ ጫካ የገቡ አካላትም በምክክር መድረኩ እንዲሳተፉና ሀሳባቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባ እና ለዚህም መንግስትም ቁርጠኝነት ማሳየት እንዳለበትም በአባላቱ መነሳቱን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡