የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ

AMN- ሚያዚያ 29/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ ከመላው ሀገሪቷ የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።

አጀንዳዎቹን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) አስረክበዋል።

አጀንዳዎቹ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰቡና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች እና በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰው፣ በቀጣይም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የበኩሉን እንደሚወጣም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፣ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች የሚታዩ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት የሚያስችል አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር እንዲደረግባቸው የማድረግ ዓላማ አንግቦ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ልዩነት በተፈጠረባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በተቋማትና በማህበረሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በአግባቡ እንደሚጠቀምባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በወንድምአገኝ አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review