የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል-የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ

AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በአሁኑ ወቅት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

መንግሥት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ለመተግበር፣ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ተመንን በገበያ እንዲመራ ለማስቻል ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እንዳሉት፣በኢትዮጵያ የቆየና ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሄንን ለማስተካከል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግና ፍላጎትን ለማስተካከል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተደርጓል ብለዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ አድርጓል ብለዋል።

በዚህም የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥተው የነበሩ መመሪያዎች ተሰባስበው አንድ ወጥ መመሪያ እንዲወጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው በኋላ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ በማውጣት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከሪፎርሙ በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ዛሬ ላይ ወደ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አድጓል ብለዋል።

ባንኮች የሚገዙትና የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ገዥ፣ ይህም ሪፎርሙ የተሳካ ሂደት ላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሀብት መጨመሩን ጠቅሰው፤ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረባቸው 518 ሚሊዮን ዶላር አሁን ላይ ከእዳ ነፃ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያዎች የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ እና ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲኖር ማስቻሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review