የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን የአብሮነት እሴት ከማጽናት ባሻገር በህገ መንግስቱና በፌዴራል ሰርዓቱ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር እድል የፈጠረ ነው፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት

AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም

ባለፉት 18 ዓመታት የተከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን የአብሮነት እሴት ከማጽናት ባሻገር በህገ መንግስቱና በፌዴራል ሰርዓቱ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር እድል የፈጠረ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችን እና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ በፌዴሬሽን ም/ቤት የመንግስት ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ህገመንግስት አስተምሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወ/ሮ ባንቺ ይርጋ መለሰ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ባለፉት 18 ዓመታት የተከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የአብሮነት እሴትን በማጎልበትና በማጽናት በህገ መንግስትና በፌዴራሊዝም ስርዓቱ የጋራ ግንዛቤ እንዲሰርጽ እና ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እንዲቀራረቡ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ እና አብሮነታቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንጡራ ሀብት የተገነባውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍፃሜ ለማድረስ ያበረከተው አስተዋጽኦ ተጠቃሽ ነው ያሉት ጸሀፊዋ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች የሚለውንም አጎልቶ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የዘንድሮው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንም “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ አስተናጋጅነት ይከበራል፡፡

በዓሉ በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድ ለማድረግ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንደሚከበርም ተመልክቷል፡፡

እንዲሁም በህዝቦች መካከል አብሮነት የበለጠ ስር እንዲሰድ በሚያደርግ ሁኔታ እንደሚከበርም ተጠቅሷል፡፡

በዓሉ ከኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ስያሜዎች እና ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን በዚሁ መሠረት፦

ኅዳር 25 “የወንድማማችነት ቀን” ተብሎ ይከበራል፣ ቀኑ በአብሮነት ሩጫ እና በባሕላዊ ስፖርት ክንውኖች ተከብሮ ይውላል።

ኅዳር 26 “የአብሮነት ቀን” ሲሆን በዕለቱ የንግድ ትርዒትና ባዛር ይዘጋጃል ተብሏል።

ኅዳር 27 “የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን” ተብሎ የሚከበር ሲሆን የክልሉን ባህሎች የሚያሳይ ፌስቲቫል እንደሚዘጋጅ ተመልክቷል።

ኅዳር 28 “የምክክር ቀን” ተብሎ የሚከበር ሲሆን በቀኑ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰላም ችቦ የሚረከቡ ሲሆን ከዚህም ባሻገር የምክክር ባህልን የማጎልበት ዓላማ ያላቸው ውይይቶች ይካሄዳሉ ተብሏል።

ማዕድ የማጋራት መርህበር እንደሚከናወንም ተገልጿል።

በሸዋዬ ከፍያለው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review