“ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገራችንን አቅምና የወደፊት ተስፋ የምናይበት ነው”

You are currently viewing “ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገራችንን አቅምና የወደፊት ተስፋ የምናይበት ነው”

                                                          የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል

በኤክስፖው ከ288 በላይ ከፍተኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ

ከ120 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙ ይጠበቃል

ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈጸማል

ቻይናውያን እ.ኤ.አ በ1860ዎቹ መጀመሪያ ላይ አሁን የደረሱበት የምጣኔ ሀብት ከፍታ ዕውን እንዲሆን ያስቻለ አንድ ዘዴ ዘየዱ፤ ይህም የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት በተሻለ ሁኔታ በመጠቀም ቻይናን ማበልጸግ እና ዓለም አቀፍ ከፍታዋን መጨመር እንደሚችሉ አቋም መውሰዳቸው ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከሽመና እስከ ማዕድን ማውጣት የዘለቀ አቅማቸውን ተጠቀሙ፡፡ ጎንበስ ብለው የምድሩን በረከት በመመልከት መስኖዎችን እና የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ለግብርና ምርቶቻቸው ከፍታ አዋሉ። በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ እና መሰል ዘርፎቻቸውም ላይ ትልቅ የለውጥ እንቅስቃሴን በሙሉ ልብ፣ ጉልበትና ዕውቀት እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት ጀመሩ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርትና ምርታማነታቸውን ጨምረው አሁን ያሉበት የምጣኔ ሀብት ደረጃ ላይ ደረሱ ትለናለች በጀርመን ሀገር የምትታተመው (DIALOUGE EARTH NEWSLETTERS) የተሰኘችው ጋዜጣ እ.ኤ.አ ሰኔ 21 ቀን 2017 “የቻይና የኢንዱስትሪ አብዮት ታሪካዊ መነሻዎች” (The historical roots of China’s industrial revolution) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገችው መረጃ፡፡

እንደ ኢትዮጵያም በ‘ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ’ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዛሬ ሚያዝያ 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ120 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህም 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈጸማል ተብሎ እንደሚገመት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል፡፡

ኤክስፖው በአዲስ አበባ በሚገኘው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ለተከታታይ አምስት ቀናት ይካሄዳል ተብሏል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት፣ በኤክስፖው ከ288 በላይ ከፍተኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከስድስት ሺህ በላይ የቢዝነስ ትስስሮች እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በዚህ ኤክስፖ የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብና መጠጥ፣ የኬሚካል፣ የስጋና ወተት፣ የማሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፋርማሲዩቲካል ምርቶች በሰባት የተለያዩ ክፍሎች ይቀርባሉ፡፡

አቶ መላኩ፣ ኤክስፖው የኢትዮጵያን አቅምና ወደፊት ተስፋ የምናይበት ነው ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር የተጀመረው ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ የተሰኘው ንቅናቄ በሌሎች ሀገራትም ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሀብት ምሁራንም ይናገራሉ፡፡ በተለይ እነ ቻይናን የመሳሰሉ ያደጉ ሀገራት የተጓዙበት፣ ብልፅግናቸውንም እውን ያደረጉበት ትክክለኛ የስልጣኔ መንገድ እንደሆነ ምሁራኑ ገልፀውልናል፡፡

በጂማ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር ለታ ሴራ (ዶ/ር) ‘ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ’ን እና ኤክስፖን አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ አንድ ሀገር ራሷ ማምረት ከቻለች ሊቀየር የሚችለው የመጀመሪያው ነገር ከውጭ ታስገባቸው የነበሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ የሚተኩበት ሁኔታ ነው፡፡

በሌላ በኩል በዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በአሉታዊ ጎኑ የሚታየው ነገር አዳጊ  ሀገራት ጥሬ ዕቃቸውን ልከው በፋብሪካ የተቀነባበሩ ብዙ ምርቶችን ከውጭ ሀገራት የሚያስገቡበት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም ‘በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ’ ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በተወሰነ መልኩም ቢሆን በሀገር ውስጥ መተካት ቻልን ማለት የውጭ ምንዛሬን እንቀንሳለን፤ ሌሎች ሀገራት ላይ የሚኖረንን ጥገኝነት በመቀነስ ሉአላዊ አምራችነታችንን እናረጋግጣለን፤ ይህም የኢኮኖሚ አቅማችንን በዓለም አደባባይ የምናሳይበትን ዕድል የሚፈጥር ንቅናቄ ነውም ብለዋል፡፡

‘ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ’ም ሆነ ኤክስፖው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን የተዛባ የንግድ ሚዛንን የማስተካከል አቅም እንደሚፈጥር የገለፁት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፣ በተለይም ንቅናቄው እየተጠናከረ በሀገር ውስጥ የምናመርታቸው ምርቶችም እየጨመሩ ሲሄዱ የግብርና ምርቶችን በተለያየ መልኩ በሀገር ውስጥ አቀነባብሮ በመላክ፣ ትልልቅ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን እሴት በመጨመርና በራስ አቅም ጭምር ወደማምረት ደረጃ ላይ ከፍ እያልን እንመጣለን፡፡ 

በዓለም ገበያም ሁሉንም ነገር ሳይሆን የምንፈልጋቸውን ውስን ነገሮች የምናስገባበት እና የራሳችንንም ምርት አቅርበን ተጠቃሚ የምንሆንበት አጋጣሚ በስፋት ስለሚፈጠር ዕድገታችንንም በዚያው ልክ ከፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ንቅናቄው ኢትዮጵያ በትክክልም ማምረት ትችላለች፣ አቅም አላት፣ የሰው ጉልበት አላት እንዲሁም ዕውቀት አላት የሚለውን ነገር በተግባር እያሳየ ነው፡፡ ኤክስፖውም ይህንን በተግባር የሚመሰክር ነው፡፡ በመሆኑም ንቅናቄው በይበልጥ እየሰፋ በብዙ ውጤትም እየታጀበ ሲመጣ የኢትዮጵያ ከፍታ ያለ ጥርጥር እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል፡፡

በዓለማችን ያደጉ ሀገራት የዕድገት ታሪካቸው የሚያሳየው ዋናው ነጥብ ሀገራቱ በራሳቸው አቅም ማምረት መቻላቸው ነው፡፡ ለአብነትም እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና እና ሲንጋፖርን የመሳሰሉት ሀገራት የዕድገታቸው ምስጢር በሀገር ውስጥ ምርታቸው ላይ የሰሩት ንቅናቄና ያመጡት ተጨባጭ ለውጥ ነው፡፡

እነዚህ ሀገራት በእድገታቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ ያደረጉት ዋናው ነገር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር በጥሩ ዋጋ በመሸጥ፣ ከውጭ የሚያስገቡትን በሀገር ውስጥ በማምረት እና በሀገር ምርት መኩራት ብሎም መጠቀምን ነው፡፡ ይህም አሁን ለደረሱበት የምጣኔ ሀብት ከፍታ እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን ቀደም ባሉት ዘመናት ታሪካችን ‘ኢትዮጵያ ታምርትን’ የመሳሰሉ ምጣኔ ሀብታዊና ሀገራዊ ንቅናቄዎች እምብዛም ባለመኖራቸው የማደግ ዕድሎቻችን ባክነዋል፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ታምርት፣ ትታይ እና ትስራ የሚሉ ሀገራዊ ንቅናቄዎች መምጣታቸው ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና እውን መሆን ትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን የሚያሳይ ስለመሆኑም የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ለታ ሴራ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

አክለውም ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ከሚለው ድንቅ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ዜጎችም ኢትዮጵያ ትጠቀም ማለት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርቶችን መግዛትና መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ምርት መኩራት ሲጀምሩ የሀገር ከፍታ ይጨምራል፤ የህንድ እና መሰል ሀገራት ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ምስጢርም የሚያሳየው ይህንኑ ሀቅ ነው ብለዋል፡፡

“የውጭ ምርት ብቻ ነው ጥሩ” ከሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን የሚሉት ለታ (ዶ/ር) ለአብነትም ለማስተማርና ለሌሎች ተግባራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ህንዳውያንን ተሞክሮ አንስተዋል፡፡ ይሄውም ህንዳዊያኑ ከሀገራቸው ሲነሱ የሚቆዩበትን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ ከሚለብሱት ልብስ ጀምሮ የሀገራቸውን ምርት ይዘው ይመጣሉ፡፡ በዚህም ኢኮኖሚያቸውን ያነቃቃሉ፣ ባህላቸውንና ምርታቸውንም ያስተዋውቃሉ፤ ከፍ ሲልም ለሀገራቸውም ዕድገት መፋጠን እንደ ዜጋ የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ፡፡ አሁን አደጉ የምንላቸው ሀገራትም የዕድገታቸው አንዱ ምስጢር ይህ ነው የሚል ነጥብ አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ በረከተአብ ዐቢይ በበኩላቸው፣ ‘ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ’ እንደ ሀገር ብዙ ፋይዳዎችን የሚያጎናፅፍ ነው፡፡ ለአብነትም ከውጭ የምናስገባውን ምርት በሀገር ውስጥ የመተካት አቅምን የበለጠ ያሳድጋል፡፡ በምርትና ምርታማነት ራሳችንን እያጎለበትን በሄድን ቁጥር ደግሞ ከፍታችን ይጨምራል ብለዋል፡፡

ንቅናቄው በመንግስት ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችም ጭምር በንቃት የሚሳተፉበት በመሆኑ ከጓሮ አትክልት ጀምሮ እስከ ትልልቅ ማሽነሪዎችና መሰል ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ዕድል ዕድገታችንን ያፋጥናል፡፡ ስለሆነም ንቅናቄው እንደ ሀገር በትኩረት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ውጤቱም ከማምረት በላይ ነው፡፡ በኮሪደር ልማቱ የምንጠቀምባቸው የመንገድ ዳር ጌጠኛ መብራቶችና መሰል ምርቶች በሀገር ውስጥ ተመርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡

ይህም ቀደም ባሉት ዓመታት ፕሮጀክት ጀምረን ቶሎ እንዳንጨርስ ከሚያደርገን አንዱ ምክንያት ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ስለምናስገባ ነው፡፡ አሁን ግን የሌላውን ዓለም ልምድ አየን፤ ያየነውን ወደ ተግባር ለወጥን፤ በውጤቱም ተጠቃሚ መሆን ጀመርን፤ ለዚህ ደግሞ በኮሪደር ልማቱ ላይ የምንመለከታቸው የመስታወት ቴክኖሎጂዎችን የተጠቀሙ ሱቆች፣  ልዩ ልዩ መብራቶች እና መሰል ምርቶች ማሳያ ናቸውም ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የበለጠ ስኬታማነት የዜጎች ተሳትፎ የጎላ ነው የሚሉት በረከተአብ፣ ለአብነትም በሀገሩ ምርት መጠቀም፣ ማስተዋወቅ፣ እንደ ሀገር ምርታማነት ከፍ እንዲል በሚችለው ሁሉ መሳተፍ እንዳለበትና ለዚህ ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መዘርጋት ኢንዱስትሪዎችን፣ ማህበረሰቡንና ተቋማት የበለጠ ማገናኘት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹትም ከሚያዝያ ከዛሬ እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከናወነው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያን ምርት ማስተዋወቅ ነው፡፡ ምርቱን ባስተዋወቅን ቁጥርም ተጨማሪ ገበያ እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩልም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በቂ ትኩረት ባለማግኘታቸው ምክንያት የሀገር ውስጥ ምርቶች በጥራትም የተሻሉ ሆነው ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የመሻት ዝንባሌ ስላለ ህብረተሰቡ በሀገር ውስጥ የመጠቀም ምርቱ እንዲያድግ ለማድረግ እንዲሁም ገበያ ትስስር ከሸማቹም ጋር ሆነ ከኢንዱስትሪዎች የእርስ በእርስ ትስስርን መፍጠርና የምርት ጥራጥን ለማሳደግ፣ ፈጠራን ለማበረታታት  ይረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማዳረስ የንቅናቄ መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አስታውሰው በዚህም ከ168 በላይ መድረኮች ተደርገው 36 ሺህ ዜጎች ተሳትፈዋል፡፡ 94 ባዛርና ንግድ ትርኢቶች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይም የምርት ግብይቶች ተከናውነዋል፡፡ ከ31 ሺህ በላይ ጎብኝዎችም ተሳትፈውበታል፡፡

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገለፃ ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ የሚለው ንቅናቄ ፋይዳው ምርት ከማምረት በላይ ነው። ለአብነትም ብዙ ፋብሪካዎቻችን ወደ ምርት ሲገቡ ሰፋፊ የስራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡ ይህም እንደ ማህበረሰብ መረጋጋትንና ተጠቃሚነትን ይጨምራል። የመንግስትም ገቢ ያድጋል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቀላሉ እንዲፈቱ ጉልበት ይሆነዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገርን እንደ ሀገር ከፍ አድርጎ ለማስቀጠል የሚያስችል ትልቅ አቅም ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንደገለፁት፣ የበለጸገች እና ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገርን ለመገንባት ኢንዱስትሪዎቻችንን በማሳደግ፤ ዐቅምን በመፍጠር ፈጠራ በታከለበት መንገድ ፈተናዎችን በማለፍ ኢትዮጵያን አንደኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ ማድረግ ይገባል፡፡

Xበመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review