የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓዙ መንገደኞች በዓለም አቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በኩል እንዲስተናገዱ አሳሰበ
AMN – ጥር 28/2017 ዓ.ም
ዛሬ ከቀኑ 6:30 በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ውስጥ ወደ በረራ ይዞ መግባት ከሚከለከሉ ቁሳቁሶች መካከል ከመንገደኞች የሚሰበሰብ የሲጋራ መለኮሻ (ላይተር) ጊዜያዊ የማስቀመጫ ስፍራ ውስጥ ጭስ በመከሰቱ ለመንገደኞች ደህንነት ሲባል ሕንፃው ለጊዜው አገልግሎት መቋረጡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።
በመሆኑም በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓዙ መንገደኞች በዓለም አቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በኩል ወደ በረራቸው እንዲሳፈሩ አሳስቧል፡፡
ከነገ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለመደው የሀገር ውስጥ ተርሚናል አገልግሎት መስጠት የሚቀጥል መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ ለተፈጠረው መጉላላት መንገደኞችን ይቅርታ ጠይቋል፡፡