
AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርበን ልቀትን የሚቀንስ ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ ለመጠቀም ወደ ስራ መግባቱን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአየር ትራንስፖርት አማካኝነት የሚከሰተውን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ዘለቄታ ያለው አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ ሁሉም አየር መንገዶች እ.አ.አ እስከ 2050 ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፤ መጪው ጊዜ በአቪዬሽን ዘርፍ ውስጥ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ የሚውሉበት ይሆናል።
ከእነዚህም መካከል በአየር ትራንስፖርት አማካኝነት የሚከሰተውን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ዘላቂና አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ መጠቀም አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለዚህም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ይህን አማራጭ ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል ፖሊሲ እየተዘጋጀና ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይ ጊዜያት የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ይህ አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችሉ ምቹ አውሮፕላኖችን የሚያመርቱ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ይህን ነዳጅ በብዛት ለመጠቀም ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
ለዚህም አንድ የአሜሪካን ኩባንያ ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ በኢትዮጵያ ለማምረት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኩባንያው ጋር ውል መፈራረሙን አስታውቀዋል።
ይህም አየር መንገዱ በኩባንያው አማካኝነት የሚመረተውን የአውሮፕላን ነዳጅ በብዛት መጠቀም እንደሚያስችለው ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ይህን አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ በተወሰኑ አውሮፕላኖች ሙሉ በሙሉና በከፊል ጥቅም ላይ እያዋለ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።