የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮንጎ ኪንሻሳ አየር መንገድን በ1 ወር ውስጥ ለማቋቋም ዝግጅት አጠናቋል -አቶ መስፍን ጣሰው

AMN – ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አየር መንገድን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚያስገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በራዕዩ መሰረት ሊደርስበት ያቀደው ደረጃ ላይ ለመድረስ በሁሉም አቅጣጫ በፈጣን የእድገት መንገድ ላይ ይገኛል።

በተለይ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በማቋቋም ረገድ አየር መንገዱ ሰፊ ተሞክሮ እንዳለውና በቅርቡም በኮንጎ ኪንሻሳ አዲስ አየር መንገድ ለማቋቋም ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ እንዲሁም የኮንጎ መንግስት 51 በመቶ ድርሻ በመያዝ በመጨው ህዳር ወር መቀመጫውን ኪንሻሳ ላይ ያደረገ አዲስ አየር መንገድ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው ያስታወቁት።

የኤር ኮንጎን አየር መንገድ የማስተዳደር ሃላፊነትም ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ የመጀመሪያ አገልግሎቱን በሁለት አውሮፕላኖች በሀገር ውስጥ በረራ እንደሚጀምርና ከስድስት ወር በኋላ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በመጨመር ወደ ጎረቤት ሀገራት በረራ ይጀምራል ብለዋል።

የኮንጎ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት የላቀ መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ገበያ ትርፋማነት ወሳኝ ስራ እንደሚሆን አንስተዋል።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች አየር መንገዶቻቸውን እንድናቋቁምላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከሃገራቱ ጋር ለመስራት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀደም ብሎ ፣ በቶጎ አየር መንገድ አስካይ ኤር ዌይስ፣ በማላዊ ማላዊ ኤርዌይስ፤ በዛምቢያ ዛምቢያ ኤር ዌይስን በማቋቋም ድርሻ ይዞ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review