ዛሬ “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ – አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ የኢኮኖሚ ልህቀት ማዕከል በሆነው አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል ማስጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ በመሆኑ አዲስ አበባ ከተማን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ፈጠራን በማበረታት፣ አመራቾችን በመደገፍ፣ ፋይናንስ በማቅረብ፣ የመስሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ መሠረተ ልማትን በማሟላት፣ አስፈላጊ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ለአመራቾች ድጋፍ በማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ማምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ስራቸው እንዲመለሱ እንዲሁም አምራቾች ምርታቸውን ለሸማቹ እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር አንዲፈጥሩ፣ ሽያጭ እንዲያከናውኑ እና አምራቾች ከፍ ባለ መድረክ ተገኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችም ይህን ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበትን አውደ ርዕይ እንዲጎበኙ እንዲሁም በሀገር ምርት በመጠቀም፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በመደገፍ እና የሀገር ውስጥ ምርት በመግዛት አምራች እንዱስትሪዎችን እንዲያበረታቱም ጥሪ አቅርበዋል።