የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ አለመግባባቶች በሰላም እና በንግግር ብቻ እንዲፈቱ ጥሪ አስተላልፋለች፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 6 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየውን የርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል።
ሲካሄድ የቆየው የ2017 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ 16 ውሳኔዎችን በማሳለፍም ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ምልዓተ ጉባዔው በቤተክርስቲያኗ፣ በሀገራዊና ወቅታዊ ዐበይት ጉዳዮች ላይ መወያየቱን እና የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡
ሲኖዶሱ በዘላቂ ሰላምና አንድነት ላይ ሰፋ ያለ ምክክር ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶች በሰላም እና በንግግር ብቻ እንዲፈቱም ቤተክርስቲያን ጥሪ ማስተላለፏን ገልጸዋል፡፡
መንግስት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እየፈጸመ የሚገኘዉን የኮሪደር ልማት ስራ እንደሚደግፍና የቤተ ክርስቲያኗ ይዞታዎችን መልሶ በመገንባት እና ምትክ ቦታ በመስጠትም ጭምር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላደረጉት ቀና ትብብርም ሲኖዶሱ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የሃይማኖት ተከታዩ ምእመናንም ቤተክርስቲያን እና መንግስት በቀጣይ በሚሰሯቸዉ የልማት ስራዎች ላይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ምእመናን የተለመደ ድጋፋቸውን በገንዘብም ሆነ በእውቀት እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ምልዓተ ጉባዔው ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ያፈነገጡ ስብከቶችን ሲሰጡ የነበሩ አባቶች ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡
ሲኖዱሱ በርክበ ካህናት ጉባኤው የተሰጡ ሹመቶችም መጽደቃቸውን አረጋግጧል፡፡
በዚህም መሰረት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ህርያቆስ የአዲስ አበባ፣ ሀድያ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን በርክበ ጉባዔው መሾማቸውን አመላክተዋል፡፡
በየሺዋስ ዋለ