AMN_የካቲት 12/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፕሪሚየር ሊጉ ቀጥሎ ከፍተኛ ትኩረት ያለው የኢትዮጵያ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ በሁለት ምድብ ተከፍሎ እንደሚደረግ የሚታወቅ ሲሆን የምድብ ለ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎችም ከዚህ ቀደም በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ከነገ ጀምሮ መደረግ ይጀምራሉ።
12 ክለቦችን የሚያሳተፉበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ በአመቱ መጨረሻ ምድቡን በበላይነት የሚያጠናቅቀው ክለብ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድግ ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የሚወርዱ ይሆናል።

ሐሙስ የካቲት 13 ንብ ከየካ ክፍለ ከተማ እና ስልጤ ወራቤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚያደርጓቸው የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች የሚጀምረው የከፍተኛ ሊጉ የምድብ ለ መርሃ ግብር አርብ የካቲት 14 ሱሉልታ ክፍለ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማና ሀላባ ከተማን ከደሴ ከተማ ሲያገናኝ ቅድሜ ነገሌ አርሲ ከኦሜድላና አክሱም ከተማ ከቦዲቲ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ የ12 ኛ ሳምንት መርሃ ግብር መገባደጃ ይሆናል።
ደሴ ከተማ ምድቡን በ23 ነጥብ እየመራ ሲሆን ነገሌ አርሲ እና ሀላባ ከተማ በእኩል 22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ሆነው ይከተላሉ።
የካ ክፍለ ከተማ ፤ ኦሜድላ ፤ አ.አ ዩኒቨርስቲና አክሱም ከተማ ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
ዘላለም አብይ