የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ ተገለጸ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ ተገለጸ

AMN – መጋቢት 25/2017

የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ተገማች የንግድ ስርዓት በመፍጠር የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ በወጪ እና ገቢ ንግድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

መንግሥት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች በማድረግ ተወዳዳሪ፣ ተገማች እንዲሁም ቀጣናውን በንግድ የሚያስተሳስሩ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስችላትን በቂ ዝግጅት በማድረግ በበርካታ መለኪያዎች ተቀባይነት ማግኘት የሚያስችላት ድርድር ማድረጓን አንስተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዋጅ ተቋቁሞ በአዲስ ከተደራጀ በኋላ የንግዱን ከባቢ ምቹ የሚያደርጉ ርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።

በበርካታ ሂደቶች የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ የንግዱን ማህበረሰብ የመደራደር አቅም በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ብዝኃ ዘርፍ የወጪ ንግድን ለማሳለጥ አጋዥ እንደሆነ ማንሳታቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review