AMN- ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም
ሁለት ተጠርጣሪዎች ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም 11 ክላሽንኮቭ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን በመኪና ጭነው ከጋምቤላ ከተማ ወደ አማራ ክልል ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ ቦንጋ ከተማ ላይ እንደደረሱ የፀጥታ አካላት በተሽከርካሪው ላይ ባደረጉት ፍተሻ በመኪና ነዳጅ ሰልቫቲዮ ውስጥ ይዘው በመገኘታቸው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ መገለጹ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር በዋለው ተጠርጣሪ ኡስማን ሀሰን ላይ የወንጀል ምርመራ ቡድን እና የወንጀል መከላከል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ጥብቅ ክትትልና ምርመራ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር መረብ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ መሀመድ አህመድ አረቡ፣ አህመድ ሙሀመድ ከበደ እና ያሲን መሐመድ ዳውድ የተባሉ ግብረ አበሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ከፌደራል ፖሊስ የተገነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በግብረ አበሮቹ ላይ በተደረገ የተጠናከረ ምርመራ ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፉትን ሰባት ክላሽንኮቭ፣ ሁለት የብሬን አፈሙዝ እና መሰል ካዝናዎችን በፍተሻ በመያዝ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ኡስማን ሀሰን አደም፣ ዘሪሁን ፀጋይ ገ/ፃዲቅ የተባለ ግለሰብ ስልክ በመጠቀም ጋምቤላ ከተማ ለሚገኘው መሐመድ ሀሰን ደውሎ በጋምቤላ ከተማ ለጦር መሣሪያ ማከማቻነት በተዘጋጀ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ የተለያዩ አይነት የጦር መሣሪያዎችን በአስቸኳይ ከቤት አውጥቶ እንዲያሸሽ እና በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ መረብ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሌሎች ግብረ አበሮች ለጊዜው ስልካቸውን በማጥፋት እንዲደበቁ መልዕክት ማስተላለፋን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እንደደረሰበትም አመልክቷል።
ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በፀረ-ሰላም ቡድኖች እጅ ቢገቡ በንፁሃን ላይ የሚያደርሱትን የከፋ አደጋ በመገንዘብ መሰል ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ሲመለከት ተቋሙ ያበለፀገውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) በመጠቀም ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመደወል በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡