የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በ31ኛ ሳምንት ይመለሳል

AMN-ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

የውድድር ቦታውን ከሃዋሳ ወደ አዳማ የቀየረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 31ኛ ሳምንቱ ዛሬ ይጀምራል፡፡

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በሚከናወነው ጨዋታ 9 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ አርባምንጭ ይገናኛሉ፡፡

መውረዱን ያረጋገጠው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቀሪ ስድስት የሊጉ መርሃግብር ጨዋታዎችን የሚያደርገው ለክብር ነው፡፡

ለአርባምንጭ ከተማ ግን ጨዋታው ወሳኝ ነው፡፡ ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ ያልሆነው አርባምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው በአምስት ነጥብ ብቻ ይርቃል፡፡

በሃዋሳ ቆይታው ጥሩ ጊዜ ያላሳለፈው አርባምንጭ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎችን ተሸንፏል፡፡ ግብም ማስቆጠር የቻለው በአንዱ ብቻ ነው፡፡

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የዋንጫ ማረፊያውን የመጠቆም አቅም ያለው ጨዋታ ይከናወናል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ለሁለቱም ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ከሌሎች ክለቦች በተሸለ የውድድር ዓመቱን በወጥነት እያሳለፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ዛሬ ካሸነፈ ከቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 12 ያሰፋል፡፡ ሊጉን የማሸነፍ እድሉንም የበለጠ ያሰፋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ካሸነፈ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱ ወደ ስድስት ይጠባል፡፡ የሊጉ ፉክክርም የበለጠ አጓጊ ሊሆን ይችላል፡፡

ሁለቱም ክለቦች በመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አራቱን አሸንፈው በአንዱ ተሸንፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቡና 2ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review