ብራዚል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ እና ብራዚል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም በሳኦ ፖሎ ተካሂዷል።
በብራዚል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በኢትዮጵያ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የብራዚል ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደር ልዑልሰገድ ታሪካዊው የኢትዮ-ብራዚል ግንኙነት ወደ ተጠናከረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሊሸጋገር እንደሚገባውም ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የብራዚል ኩባንያዎች መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው በግብርና፣ በማምረቻው ዘርፍ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች ቢሰማሩ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በፎረሙ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዮሐንስ ፋንታ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና የመንግሥት ፖሊሲ ዙሪያ ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል።
በብራዚል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አንቶኒዮ ሴዛር በበኩላቸው ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡