AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ብራዚል የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም ትስስር ማጠናከር፣ በግብርና፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መስኮች ያሉትን እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም እና የኢትዮ-ብራዚልን የወዳጅነት ግንኙነትን ይበልጥ ለማዳበር ከመግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
ሦስተኛው የኢትዮ-ብራዚል የፖለቲካ ምክክር በብራዚል ዋና ከተማ ብራዚሊያ ተካሂዷል።
በምክክሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እና በብራዚል ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ዋና ኃላፊ አምባሳደር ካርሎስ ዱአርቴ የተመራ ልዑካን ተሳትፏል።
በፖለቲካ ምክክሩ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ዘርፎች ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።
በቀጣይ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ የቱሪዝም ትስስር ማጠናከር፣ በግብርና፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መስኮች ያሉትን እድሎች በአግባቡ ለመጠቀምና የኢትዮ-ብራዚልን የወዳጅነት ግንኙነቱን ይበልጥ ለማዳበር ከመግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
ሀገራቱ ስለሚገኙባቸው ቀጣናዊ ጉዳዮች የሃሳብ ልውውጥ በማድረግ፣ ብሪክስን ጨምሮ በዓለም አቀፍ መድረኮች በአየር ንብረት ለውጥ፣ አካታች የዓለም ስርዓት መፍጠር አስፈላጊነት፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤትና በፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያዎችን በሚመለከት በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።
በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠራቸውን መልካም እድሎች በዝርዝር በማስረዳት፣ የብራዚል ባለሃብቶች በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ በስፋት እንዲሳተፉ አምባሳደር ምስጋኑ ግብዣ አቅርበዋል።
የሚቀጥለው የፖለቲካ ምክክር በአዲስ አበባ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።