AMN- ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የኦስትሪያ ቢዝነስ ፎረም ነገ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ፎረሙ ኢትዮጵያና ኦስትሪያ በኢኮኖሚው ዘርፍም ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩበት ነው ብለዋል።
በፎረሙ ትልቅ ልምድ ያላቸው የተለያዩ የኦስትሪያ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዕድል የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በቢዝነስ ፎረሙ በጤና እንዲሁም በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
የሚሳተፉ ኩባንያዎች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በነገው ዕለት ለሚደረገው የቢዝነስ ፎረም ኩባንያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ፎረሙን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዲስ አበባ ከሚገኘው የኦስትሪያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።