የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀድሞ አባሉ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

AMN – ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከልጅነት እስከ እውቅት የሕይወት ዘመናቸው በመንግሥትና በግል ተቋማት ማገልገላቸውን ያመለከተው ምክር ቤቱ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው በሰሩበት ወቅትም ሀገራቸውንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በትጋት፣ በቅንነትና በታታሪነት ማገልገላቸውን አመልክቷል፡፡

ወደ ፖለቲካው ዓለም ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮም የሚወዷትን ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በኃላፊነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገላቸውን ጠቅሷል፡፡

በ1997 ዓ.ም በተካሄደው 3ኛው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ የኦፌኮ ፓለቲካ ፓርቲን ወክለው በምዕራብ ወለጋ ዞን በእናንጎ ቢላ ምርጫ ክልል ለፌዴራል ምክር ቤት ተወዳድረው በማሸነፍ የሶስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ከ1998 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም) አባል በመሆን ለሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር አስተዋፅኦ አድርገዋልም ብሏል፡፡

በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን በነበራቸው ቆይታ ምክር ቤቱ በሚያካሂዳቸው ጉባኤዎች ላይ በሳልና ጠንካራ ሃሳቦችን በማንሳት የዜጎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ፈጥነው እንዲመለሱ ጉልህ አበርክቶ እንደነበራቸውም አብራርቷል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በቀሪ የሕይወት ዘመናቸውም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብሮነትና ለፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርቦ መስራት ሚዚናዊና ምክንያታዊ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቁ ለኢትዮጵያ ቅን አሳቢ አባት ነበሩ ሲልም ምክር ቤቱ አመልክቷል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለርትዕና ለፍትህ በሙሉ ልብ የታገሉ በሳል ፖለቲከኛና የዘመናችን አርበኛ ነበሩ ያለው ምክር ቤቱ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀድሞ አባሉ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሀዘን ይገልጻልም ብሏል፡፡

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን መመኘቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review