የኤም ፖክስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚከናወነው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ

You are currently viewing የኤም ፖክስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚከናወነው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
  • Post category:ጤና

AMN ግንቦት 20/2017

የኤም ፖክስ (M pox)ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚከናወነው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የኤም ፖክስ ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ133 አገራት በአፍሪካ ደግሞ በ29 አገራት መከሰቱን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በሞያሌ አካባቢ የሚኖር የ21 ቀን ህጻን በበሽታው መያዙ መለየቱን ጠቅሰው፤ በህጻኑ እናትና አባት ላይ በተደረገ የናሙና ምርመራ በሽታው እንዳለባቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።

በበሽታው የተያዙት ሰዎች በለይቶ ማቆያ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ህሙማኑ በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴሯ ከህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ድንገተኛ ምላሽ መሽጫ ማዕከል በማቋቋም የመለየት እና የቅኝት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በድንበር አካባቢ ፣በአየርና በየብስ መውጫ እና መግቢያ በሮች የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

ከንክኪ ልየታ አኳያም የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ፤ የላብራቶሪ አቅምን በማሳደግና አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ በማሟላት የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የፈጣን ምላሽ ቡድን መቋቋሙን ጠቁመው ቡድኑ በተለያዩ ክልሎች እንዲሰማራ መደረጉን ገልጸው፤ በሁሉም ክልሎች በሽታውን አስቀድሞ የመከላከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተለያዩ አውታሮች ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃንም የሚጠበቅባቸው ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review