የኤስያ-አፍሪካ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ስራዎችን ለማጎልበት የሚደረጉ ትብብሮችን መደገፍ ይገባል:- በለጠ ሞላ [ ዶ/ር ]

AMN – ታኅሣሥ – 11/2017 ዓ.ም

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ዶ/ር የኤስያ-አፍሪካ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ስራዎችን ለማጎልበት የሚደረጉ ትብብሮችን መደገፍ እንደሚገባ አስገነዘቡ ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኤስያ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት (Asian-African Chamber Of Commerce And Industry (AACCI) ጋር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።

ውይይቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በኤስያና አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ዶ/ር ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ፈጠራን እና ዘላቂ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የሀገሪቱ የእድገት ስትራቴጂ ምሰሶዎች ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለስታርታፖች፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለምርምር እና ልማት እንዲሁም ከአለም አቀፍ አካላት እና ከግሉ ሴክተር ተዋናዮች ጋር ያለውን አጋርነት ጨምሮ ለጠንካራ የፈጠራ ስነ-ምህዳር ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የኤስያ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶ/ር ጂዲ ሲንግ ኢትዮጵያ በኢኖቬሽን ጥሩ የሚባል ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን በመጥቀስ ይህንን እድል በመጠቀም በጋራ ለመስራት ምክርቤቱ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል።

በቅርቡ ቢሮውን በአዲስ አበባ የከፈተው የኤስያ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት በቀጠናው ያሉትን ቁልፍ ጉዳዮች ለመፍታት፣ ለንግድ ማህበረሰብ ስኬታማነት አንድ ወጥ የሆነ ድምጽ እና ስትራቴጂካዊ መሳሪያ ለማቅረብ፣ ከተባበሩት መንግስታት የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማጣጣም ልማትን ለማጎልበት የሚሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገነነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review