የእስራኤልና ሃማስ ስምምነት እስረኞችን በመለዋወጥ ተግባራዊ መደረግ ጀመረ

AMN-ጥር 12/2017 ዓ.ም

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን በዚህም ሃማስ ሶስት ታጋቾችን ሲለቅ በምላሹ እስራኤል ዘጠና የፍልስጤም እስረኞችን መፍታቷን አስታውቃለች።

ፍልስጤማውያኑ እስረኞች ኦፈር ከተባለው እስር ቤት በመውጣት በቤይቱኒያ ከዘመዶቻቸው ጋር ሲገናኙ ደስታቸውን ገልጸዋል።

በሀማስ የተለቀቁት ታጋቾች የ31 ዓመቷ ዶሮን ስታይን ብሬቸር፣ የእንግሊዝና እስራኤል ዜግነት ያላት ኤሚሊ ዳማሪ እና ሮሚ ጎነን የተባሉ ሶስት ሴቶች በቴል አቪቭ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተነግሯል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ስምምነት መሰረት በሃማስ ለታገቱ ለእያንዳንዱ ታጋች 30 የፍልስጤም እስረኞች ከእስራኤል እስር ቤቶች ይለቀቃሉ ተብሏል።

ስምምነቱን ተከትሎ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በመመለስ የምግብ እና የህክምና ዕርዳታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review