የእውቀት ቤቶቹ የፈጠራ ስራ

ከሳር ላይ ነዳጅ ማውጣት የቻለው ተማሪ በሳይንስ ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል

የከተማ አስተዳደሩ ለፈጠራ እና ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ትኩረት አድርጓል፡፡ ይህን ለማሳካት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስ የፈጠራ ስራ ውድድር ይጠቀሳል፡፡

በከተማ ደረጃ “በፈጠራ ስራ የተካነ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና” በሚል ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ በተካሄደው 10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስ የፈጠራ ስራ ውድድር የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ አሸናፊ ያደረጋቸው ምስጢር ምንድነው? የሚለውን የክፍለ ከተማ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊን በማነጋገር እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት መምህራን እና ተማሪዎችን ከመደበኛው መማር ማስተማር በተጨማሪ በሳይንስና ፈጠራ ስራ ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ በከተማ ደረጃ በክፍለ ከተማው በሚገኙ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ተወዳድረው ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በጋራ ጉሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተማሪ ናፊስ ባይሳ በትምህርት ቤቱ አዲስ የሂሳብ ትምህርት ቀመር ወይም ፎርሙላ ፈጥሮ በማስተዋወቅ በከተማ ደረጃ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ የሂሳብ ቀመሩ ከአሁን በፊት በሌሎች ተግባራዊ ያልተደረገ ሲሆን ከሚማሩት የሂሳብ ትምህርት ጋር አያይዞ እንዴት በአጭር መንገድ ስኩየር ሩት በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ማስተዋወቅ መቻሉን ገልጿል፡፡ ለቀጣይም የፈጠራ ስራውን በማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰራ ተማሪ ናፊስ ተናግሯል፡፡

በትምህርት ቤቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሂሳብ መምህር የሆኑት መምህር ኢቤሳ ጃለታ የልዩ ፍላጎት ለአካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ የሚሆን አርቴፍሻል እጅና እግር በፈጠራ ሰርተዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ አጋዥ እንዲሆናቸው በማሰብ ከአካባቢው ቁሳቁስ የሰውሰራሽ የአካል ድጋፍ መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በፈጠራ ስራቸውም በከተማ ደረጃ ካሉ ትምህርት ቤቶች ተወዳድረው አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም ተሸላሚ መሆናቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረላቸው መምህር ኢቤሳ ገልጸዋል፡፡

በጋራ ጉሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አበበ በቀለ ትምህርት ቤቱ በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሰርተው በመወዳደር አሸናፊ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

አሸናፊ የሚያደርጋቸውን የፈጠራ ስራ ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ ቀድሞ በማዘጋጀት  መወዳደር ችለዋል፡፡   በልዩ ፍላጎት፣ በሳይንስ ዘርፍ፣ በሂሳብ፣ በአካባቢ ሳይንስ የፈጠራ ስራ ትኩረት በማድረግ ተማሪዎችና መምህራን በፈጠራ እና ሳይንስ ዘርፍ መወዳደር መቻላቸውን ርዕሰ መምህር አበበ ገልጸዋል፡፡

በፈጠራ በተማሪዎችና በመምህራን የልዩ ፍላጎት የአካል ድጋፍ፣ የቡና መፍጫ ማሽን፣ የሊጥ ማቡኪያ፣ አዲስ የሂሳብ ቀመር፣ የከተማዋን አጠቃላይ የመሰረተ ልማት እና ዘመናዊ  የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ያካተተ ንድፈ ሃሳብ በወረቀት ላይ  በማዘጋጀት ተወዳዳሪ መሆን ችለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በፈጠራ ስራው የዋንጫ እና ሌሎች የማበረታቻ ሽልማት ማግኘት መቻሉን ርዕሰ መምህሩ ጠቁመዋል። ለፈጠራ ስራው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ፣ ሱፐርቫይዘሮችና የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት አጋዥ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ተማሪ አናኒያ ባብል በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በሳይንስ ዘርፍ ታጭዶ በተሰበሰበ ሳር ላይ ነዳጅ በማውጣት ተወዳድሮ ማሸነፍ ችሏል፡፡ በኮሪደር ልማት አካባቢ ታጭዶ ተከምሮ የሚያየውን ሳር ወደ ጥቅም ላይ ለማዋል ሃሳብ በማፍለቅ የጀመረው ተማሪው ከዚህ የታጨደ ሳር ነዳጅ በፈጠራ ማግኘት እንደቻለ ተናግሯል። ከአሁን በፊት ከሸንኮራ አገዳ ነዳጅ ማግኘቱን ገልጾ አሁን ደግሞ ከሳር ነዳጅ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ የፈጠራ ስራውን ሃሳብ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ሀብት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርግ እና የፈጠራ ስራውን በማሳደግ ተሞክሮውን ለሌሎች ጓደኞቹ እንደሚያጋራ ገልጿል፡፡

መምህርት እመቤት ሞገስ በትምህርት ቤቱ ከ9 እስከ 11ኛ ክፍል የኬሚስትሪ መምህርት ናት፡፡ በሳሙና አመራረት ዘርፍ ተወዳድራ ማሸነፍ መቻሏን ተናግራለች፡፡ ሳሙና በብዙ ቦታዎች ተሰርቷል የምትለዋ መምህሯ ሆኖም ጥራቱን የጠበቀ ሳሙና ማምረት ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጻለች፡፡ ጥራቱ ያልተጠበቀ ሳሙና መጠቀም ለሰውነታችን ቆዳ አላርጅክ እንደሚፈጥር ጠቁማ ይህን ለማስቀረት ከተፈጥሮ ነገሮች ጥራቱን የጠበቀ ሳሙና ማምረት መቻሏን ተናግራለች፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ጣሳቸው ጫኔ በትምህርት ቤቱ በየዓመቱ አዳዲስ የፈጠራ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው ባለፈው ዓመት በነበረው የሳይንስ የፈጠራ ውድድር ሶስት ዋንጫዎችን ማግኘት እንደቻሉ ገልፀዋል።

በዚህ ዓመት የፈጠራ ስራ ለመስራት ትምህርት ቤቱ  በሃሳብና በግብዓት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በመምህራንና በተማሪዎች  የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች  መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኬሚስትሪ ዘርፍ ደረቅ ሳሙና እንዴት ማምረት ይቻላል የሚለውን ሃሳብ በማፍለቅ በተግባር  በመምህራን ተሰርቷል፡፡ በቅርጻቅርፅ  ስራ፣ በአይሲቲ ዘርፍ በትምህርት ቤት አስተዳደር እንዲሁም  የቦቆሎ መፈልፊያ ማሽን እና ድሮን በመስራት  ተወዳዳሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከሳር ነዳጅ ማምረት፣ በስእል፣ በሂሳብ ትምህርት ፎርሙላ አዳዲስ የፈጠራ ዘርፍ መወዳደር ችለዋል፡፡

እንደ ርእሰ መምህር ጣሳቸው ገለጻ በትምህርት ቤቱ በየጊዜው የመምህራንና የተማሪዎች ፈጠራ ስራ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የፈጠራ ስራቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ የቆየ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቁመው ከአሁን በፊት በትምህርት ቤቱ ድሮን የሰራ አንድ ተማሪ አሁን በአሜሪካን ሀገር ቴስላ የመኪና ካምፓኒ ውስጥ ተቀጣሪ መሆን መቻሉን ርእሰ መምህሩ ገልጸዋል፡፡

የሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ በርካታ ጠቀሜታ የሚያስገኝ መሆኑን ርዕሰ መምህር ጣሳቸው ገልጸው ተማሪዎች ችግር ፈቺ መሆናቸው በቀጣይ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ስራ ፈላጊ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሀገር በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ ማተኮር ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ርዕሰ መምህሩ  ተናግረዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ለሊስቱ ተስፋዬ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት “በፈጠራ ስራ የዳበረ ትዉልድ ለሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና“ በሚል መሪቃል በከተማ ደረጃ በተካሄደው ውድድር አሸናፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ ለተከታታይ አራት ዓመታት ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ተናግረዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት መምህራንን እና ተማሪዎችን ከመደበኛው መማር ማስተማር በተጨማሪ በሳይንስና ፈጠራ ስራ ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ በ10 ወረዳዎች በሚገኙ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቻቸውን አቅርበው እንዲወዳደሩ  መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የሚገኙ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን በየዓመቱ የተለያየ የፈጠራ ስራ እንደሚያቀርቡ ገልጸው ትምህርት ቤቶቹን ከክፍለ ከተማ ጀምሮ በወረዳ እና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ ጋር ተከታታይ ድጋፍና ክትትል በማድረግ አዳዲስ የፈጠራ ስራ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ክፍለ ከተማውን የፈጠራ ማእከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በከተማ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ ተወዳድረው የዋንጫ እና ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ለሊስቱ ገለጻ በመምህራን እና ተማሪዎች በሳይንስ ዘርፍ በፊዚክስ፣ ሂሳብ፣ ባዮሎጂ፣ በኬሚስትሪ፣ በልዩ ፍላጎት፣ በአይሲቲ፣ በሮቦት፣ በኮምፖስት ዝግጅት፣  የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሳር ውሐ ማጠጣት የፈጠራ ስራ ዘርፍ ስራቸውን ይዘው በመቅረብ ተወዳድረው አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡

የፈጠራ እና ሳይንስ ዘርፍ ለመማር ማስተማሩ ዘርፉ አጋዥ መሆኑን ጠቁመው የንድፈ ሃሳብ ትምህርትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች የንድፈ ሃሳብ ትምህርትን ወደ ተግባር ትምህርት ፈጠራ ስራ በመለወጥ ልጆች በራሳቸው ተመራምረው የተሻለ ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ  እንደሚያግዛቸው ወ/ሮ ለሊስቱ ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የሳይንስና ፈጠራ ስራ ትኩረት መሰጠቱ ሀገሪቱ በሳይንስ እና ፈጠራ ዘርፍ እንዲሁም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስኬታማ እንድትሆን እንደሚያስችል ኃላፊዋ ተናግረዋል። በትምህርት ቤቶች የፈጠራ ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው እና በሂደት ላይ ያሉ የፈጠራ ስራዎች እንዲመዘገቡ እንደሚያደርጉ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review