ከከተሜነት ፅንሰ ሃሳብ መለኪያነት አንፃር አንድ ከተማ በትክክል የከተሜነትን መስፈርት አሟልታለች ተብሎ እውቅና የሚሰጣት በአንደኛ ደረጃነት የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም እና የትራንስፖርት አገልግሎት መሰረት ልማቶችን ስታሟላ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የአረንጓዴ ሽፋን፣ የከተማ ውበት እና ንፅህና ደግሞ በሁለተኛ ደረጃነት የሚለኩባቸው መስፈርቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት፣ በዓለም ላይ ያሉ ከተሞች የሚለኩበት የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ሽፋን ስታንዳርድ 30 እጅ እንዲሆን ቢጠበቅም ጥናቱ በተደረገበት ወቅት የከተማችን የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ሽፋን ከ2.8 አይዘልም ነበር ብለዋል።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘንድሮውን ሳያጠቃልል ሽፋኑን ከ20 እጅ በላይ ማድረስ መቻሉንና በአጭር ጊዜ ወደ 30 እጅ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
በስታንዳርዱ ከሚታዩ መካከል መፀዳጃ ቤቶች እና የህዝብ መገልገያ ስፍራዎችም የሚካተቱ ሲሆን፣ በዚህም ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ እንደሆነና ቃል በተገባውም መሰረት አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አዲስ አበባ እናደርጋታለን የሚለውን እየተገበርን ነውም ብለዋል።