የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ ስራ አለማድነቅ ንፉግነት ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋት መልዕክት፤ የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እስካሁን በከተማዋ ከተገነቡት የኮሪደር ልማት ስራዎች በውስጡ ባስተሳሰራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የተለየ ገፅታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቀደመውን የአካባቢዉን ምስቅልቅል ሁኔታ በአይነ ህሊናው ለሚያይ፣ በተለይ በዕለት ተዕለት ህይወቱ አከባቢውን ሲያስተውል ለነበረ የከተማው ነዋሪ በኮሪደር ልማቱ የተፈጠረው አዲስና ውብ ገፅታ በምናብ ከሚያውቀው የውብ እይታና ሀሴት ነፀብራቅ ተምሳሌት ከሆነው የገነት ፀዳል አንዳች ሀሳብ ተውሶ ከተማችንን ወደ ምድራዊ ገነት እየቀየርናት ይሆን? ብሎ እንዲጠይቅ ያነሳሳል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህን የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ የካዛንችስን ድንቅ ስራ አለማድነቅ ንፉግነት ነው ሲሉን ገልጸዋል ሚኒስትሩ፡፡

ከሰሞኑም የከተማችን ሰው ተኮርና ሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ አካል የሆነው የካዛንቺስ ኮሪደር ልማት፣ በ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን ውብ በማድረግ አካባቢውን ካላበሰው አዲስ ገጽታ ባሻገር በዘመናዊነቱም ይጠቀሳል ነው ያሉት።
ለአዕምሮ ሀሴትን የሚፈጥሩና ለእይታ የሚማርኩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ጽዱ አካባቢን ለነዋሪው በመለገስ ሌላ አዲስ ተጫማሪ የመዝናኛ ስፍራን ለከተማዋ፣ በተለይም ለነዋሪዎቿ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋንም ገጽታ አንድ ደረጃ ክፍ ያደረገው ይህ ግንባታ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ትንሣኤ አይቀሬ መሆኑንም ያመላክተ ነውም ብለዋል፡፡
ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ (smart city) አካል በመሆኑ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታችን ሞዴል ተደርጎ የሚወሰድም ነው ያሉት ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ ኮሪደሮች ትስስር እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የከተማዋ ገጽታ በመሰረታዊነት እየተቀየረ መሆኑን ማየታቸውን አውስተዋል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና “አዲስ አበባ” እያደረጓት ነው ሲሉም አስፍረዋል፡፡
ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች መስፋፋታቸው እና የተሳለጡ መሆናቸው ለኮሪደር ልማት ስራዎች እንደ ጀርባ አጥንት የሚቆጠሩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ እነዚህ ግንባታዎች የሰውና የተሽከርካሪ መጓጓዣ መንገዶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፤ የመብራት፣ የስልክ እና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራዎች ወዘተ የሚያካትቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
መሰረተ ልማቶቹ በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስተሳሰር በሁሉም አቅጣጫ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸውም ብለዋል፡፡ በመሠረተ ልማቶቹ ዝርጋታም ሆነ በመልሶ መልማት ከቦታው የሚነሱ ነዋሪዎች የሚዛወሩባቸውን የመኖሪያ መንደሮች ጭምር የሚያካትቱ ናቸው በማለት መኖሪያ መንደሮቹ ዘመናዊ ከመሆናቸው ባሻገር ለነዋሪዎች እንዲመቹ እንደ ትምህርት ቤት፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የዳቦና እንጀራ መጋገሪያ እንዲሁም የአቅመ ደካሞች መመገበያ ማዕከሎችን ያካተቱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ልማቱ ሁሉን አቀፍ፣ አካታች እና ሰው ተኮር ነው የሚባለውም ለዚሁ እንደሀነ ገልጸዋል።
የመዝናኛ ስፍራዎቹ ከማዝናናት ባሸገር አዕምሮን ለማሳረፍ፣ ከራስ ጋር ለመታረቅ፣ በንባብ አዕምሮን ለመገንባት፣ በስፖርት አካልን ለማበልፀግ ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ የአረንጓዴ ስፍራዎች ከአካባቢያቸው ጋር የተስማሙ ዘላቂ የከተማ ልማት (Sustainable and environmentally friendly cities) የመገንባት አቅጣጫን የተከተሉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ይህን ዘመናዊ፣ ሁሉን አካታች፣ ቅርስን በማቆየት ለዛሬው የተመቸ፣ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆነንን አኩሪ ስራ አንዳንድ ሰዎች ባለማወቅም ይሁን ሆን ብለው “ብልጭልጭ ነገር” ብለው ሊያሳንሱት ሲሞክሩ ይታያል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ ሰብዓዊነት ለምን አይቀድምም ሲሉ ይደመጣል በማለት የገለጹት ሚኒስትሩ መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ትችቶቹ ከሰው ተኮር ልማቱና አገርን በማበልፀግ ህዝብ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለማድረግ ከተያዘው መሠረታዊ መርሆዎች ያፈነገጡ ናቸው ብለዋል።
ምክንያቱም የአንድ ከተማ ዕድገት ቁልፍ መለኪያ የሚባሉት ከላይ በዝርዝር የቀረቡ መሠረተ ልማቶች ምን ያህል አካታች በሆነ መንገድ ተሟልተዋል? ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ አግልግሎት ቀርቧል ወይ? የሚለው መሆኑን አብራርተዋል።

ትችቱ፣ ከቁልፍ መሠረተ ልማቶቹ አንዱ በሆነው የመንገድ ዳር መብራት ጉዳይ የሚቀርብ ከሆነም እሱም ስህተት ነው፤ ምክንያቱም በጣም አድጓል ተብለው ለከተሞች ደረጃ ለመፈረጅ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መሥፈርቶች አንዱ በሌሊት ከተሞቹ ከሳተላይት በሚወሰዱ መረጃዎች ምን ያህል ብርሃናማ ናቸው የሚል ነው ብለዋል።
ብርሃን በእጅጉ ደምቆ የሚታይበት ከተማ ብቁ መሠረተ ልማት ያሟላና ያደገ ተደርጎ ይወሰዳል ያሉት ሚኒስትሩ ነዋሪዎቹም ደስተኞች ሆነው የሚኖሩበት፣ ወንጀል በስፋት የማይታይበት እና የብልጽግና ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉም ነው ያሉት። በአንጻሩ በጭለማ የተዋጡ ከተሞች መሠረተ ልማት ያልተገነቡላቸው፣ ወንጀል የሚበዛባቸው፣ ነዋሪዎቹም በምቾትና በደህንነት ከመኖር አንፃር ተስፋ የሚያጡባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መጀመሪያ ሰብአዊነት አይቀድምም ወይ ለሚሉት ደግሞ ምላሹ ከዚህ የተሻለ ምን አይነት ሰብአዊነት አለ የሚል ነው፤ እጅግ ለመኖር አስቸጋሪ ከሆነና ከተጎሳቆለ አካባቢ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ ስፍራ ከማይገኝበት፣ ሰው እና ተሽከርካሪ እየተጋፉ ከሚጓዙበት ውስብስብና ጭንቅንቅ መንገዶችና አከባቢዎች በመውጣት እነዚህ ጉዳዮች በተሟሉበት ከባቢና አውድ መኖር እንዴት ሰብዓዊነትን ማጣት ይሆናል? ሲሉም ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አዛውንቶች መውጫና መግቢያ አጥተው ከሚንከራተቱበት፣ በደሳሳ ጎጆ እንዲታፈኑ ከተገደዱበት፣ ህፃናትና ወጣቶች ለማህበራዊ ጠንቆች ከሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ተነጥለው ለመኖር እጅግ ምቹ ወደ ሆኑ የተቀናጀ ማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸው፣ የተሻሻለ የኑሮ ዘይቤ ወደሉባቸው አካባቢዎች መዛወራቸው እንዴት ሰብዓዊነትን መፃረር ተደርጎ ይወሰዳል? ሲሉም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
ይህ የሰብዓዊነት መለኪያውስ ምን ይሆን ያስብላል። ዜጎችን በተሻለ የህይወት ደረጃና ጤንነት እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ ምንስ ሰብአዊነት አለ? ብሎ ህሊናን መጠየቅ ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
ለነገሩ ከተቺዎቹ በላይ ህዝቡ፣ በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከካዛንቺስ ኮሪደር ልማት አስቀድመው የካዛንቺስ ልማት ተነሺዎች አዲስ ህይወት በጀመሩበት የገላን ጉራ አካባቢ ነዋሪዎቹን ባገኙበት ወቅት ነዋሪዎቹ ያሳዩት የማይረሳ የደስታና ሀሴት ብስራት ገላጭ መልዕክት እውነታውን አሳውቆናል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በተለይ ምክንያት አልባ በሆነ የሁልጊዜ ጨለማ እይታ የሚተቹ ወገኖች መገንዘብ ያለባቸው ጉዳይ የከተማ ነዋሪዎችም እንደ የትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ብቁ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን የማግኘት እና ምቹ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያላቸው መሆኑን ነው ብለዋል።
ለራስ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ሌላውን ደፍቆና አሳንሶ እንዲኖር ማድረግ ህሊና ቢስነት ነው፤ ዜጎች በራሳቸው እንጡራ ሃብት እና ከራሳቸው በሚሰበሰብ ግብር አካባቢያቸውን የማልማት መብት እንዳለቸው ልብ ሊባል ይገባል ሲሉም አውስተዋል፡፡
በጥቅሉ ከአዲስ አበባ የምንወስደው ተሞክሮ የኮሪደር ልማት ስራ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ዜጎች ተቺዎችን ወዲያ ብለው ከአስተዳደራቸውና ከጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅተው እንዲሁም እጅ እና ጓንት ሆነው ሰላማቸውን በማስከበር መልማት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
መለስተኛ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ያሉ ወገኖቻችንም እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞቻችንን ፈልግ የመከተል እና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት መጠበቅ ግዴታ አለባቸው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ይህንን ሲያደርጉም ልማታቸው እየተፈጠነ፣ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ይሄዳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡