የከተማውን ሠላምና ፀጥታ ስጋት ላይ የሚጥሉ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እንደሚያደርግ ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing የከተማውን ሠላምና ፀጥታ ስጋት ላይ የሚጥሉ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እንደሚያደርግ ፖሊስ አስታወቀ

AMN- ግንቦት 26/2017 ዓ.ም

የከተማውን ሠላምና ፀጥታን ስጋት ላይ የሚጥሉ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እንዲሁም ሌሎች የወንጀል ስጋቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና አጥፊዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

መላው የፀጥታ አካላትና ነዋሪው በመተባበር ባከናወኗቸው ተግባራት የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ በመረጋገጡ ህብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ተግባሩን ያለ ስጋት ማከናወን እንዳስቻለው የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ በላኩት መረጃ ገልጸዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ አካባቢውን በተራ በመጠበቅ እና ህገ-ወጦችን እጅ ከፍንጅ ይዞ ህግ ፊት የማቅረብ ልምዱ እያደገ በመምጣቱ እና የፀጥታ አካላትም ባከናወኗቸው ልዩ ልዩ ተግባራት በአዲስ አበባ የወንጀል ቁጥርን መቀነስ እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ይህንን ድጋፍ እና ተባባሪነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፖሊስ በደረሱት ጥቆማዎች እና በጥናት የለያቸው ወንጀሎችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና አጥፊዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የወንጀል ድርጊቶቹ ይፈፀምባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ እና በተለዩ በሁሉም አካባቢዎች የህግ አግባብን ተከትሎ ፍተሻና ብርበራ የሚያደረግ መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ እና ወንጀል እንዳይፈፀም ነዋሪው ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ህብረተሰቡ የተለመደውን ጥቆማ የመስጠት ተግባር በማጠናከር ለማንኛውም ፖሊሳዊ መረጃ 011-1110111 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 እና 8882 ላይ በመደወል መረጃና ጥቆማ እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review