የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል ጭብጥ በተካሄደው የ2025 ፒ4ጂ ቬትናም ጉባኤ ላይ ከመሳተፍም ባለፈ ንግግር አድርገዋል፡፡ ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ምን ምን ጉዳዮችን አነሱ? ከቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ምን ተወያዩ? ፒ4ጂ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ቀጣይ አዘጋጅ ሆና ስለመመረጧ የሚሉትን እንደሚከተለው በአጭሩ ቃኝተናቸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2025 ፒ4ጂ ቬትናም ጉባኤ ላይ ስለ አየር ንብረት ለውጥ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸውም ለአየር ንብረት ጥበቃ የገንዘብ አቅርቦትን ቅድሚያ በመስጠት በቂ፣ ተገማችና ዘላቂ ምንጮች ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ቬትናም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር እያደረገች የምትገኘውን ትብብር ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ ተጽዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ ቁርጠኛ ውሳኔ የምንወስንበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ እና የአኅጉሩን ወሳኝ ሥነ ምኅዳር ጥበቃ ለማድረግ በዓለም የኃይል ምንጭ ኢንቨስትመንት ሽፋን ውስጥ የአፍሪካን ድርሻ በአሁኑ ወቅት ካለበት ሁለት ከመቶ በ2030 ወደ ሃያ ከመቶ ማሳደግ ይገባናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ይህ እቅድ በቁርጠኝነት መተግበር አለበት። ሀገራትም በእድገት እቅዳቸው ውስጥ ማካተት ይኖርባቸዋል፡፡ በአረንጓዴ ልማት ኢንሼቲቮች ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲን ማካተት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በ2050 የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል፡፡
ዘላቂ የልማት እና የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ግቦች ለማሳካት ዓለም አቀፍ አጋርነት እና የተቀናጀ አካሄድ ይጠይቃል። በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ተፅዕኖ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት የሚደረጉ ድጋፎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሊደረጉ ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የብዝሃ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡ ይህም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ሕዝባዊ ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍ፣ በዚህም ለየአካባቢው ኅብረተሰብ ከአድልዎ የፀዳ ፍትኀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ያካትታል ብለዋል።
አረንጓዴ አሻራን በተመለከተ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቬትናሙ መድረክ ኢትዮጵያ በተከታታይ ዓመታት እያከናወነችው ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሞክሮነት በጠቀሱበት ንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ በዚህ መርሃ ግብር እ.ኤ.አ ከ2019 ወዲህ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች፡፡ ይህ ዝም ብሎ የተሳካ ሳይሆን በየዓመቱ 20 ሚሊየን ዜጎችን በማሳተፍ ነው ሲሉ ልምዱን ለዓለም አጋርተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት መልክዓ-ምድርን በደን ከመሸፈን የዘለለ ዓላማ ያለው ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ውስጥ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል ከምግብ ዋስትናም ባለፈ ለውሃና አፈር ጥበቃ ትልቅ አበርክቶ እያደረግን ነው፡፡ በዚህም ከ2019 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ብቻ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአስደናቂ ሁኔታ በ6 ነጥብ 4 በመቶ ጨምሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከአጠቃላይ የሃይል ፍጆታዋ 98 በመቶውን ከሃይድሮ ፓወር፣ ከነፋስና፣ ከጸሃይ ሃይል እየተጠቀመች መሆኑን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ግድቡ ቀጣይነት ያለው እድገት ማሳያ ምልክት ነው፡፡ ይህም ማህበራዊና ኢኮሚያዊ ጠቀሜታው ከሀገር አልፎ ለቀጠናው የሚበቃ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ትራንስፖርትን በተመለከተ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በትራንስፖርት ዘርፍ እየተሰራ የሚገኘው ስራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከተሰሩ ሪፎርሞች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የነዳጅ መኪናዎችን ቁጥር በመቀነስ የኤሌክትሪክ መኪና ለሚያመርቱ ማበረታቻ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በተመለከተ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የከተማ ግንባታችን አረንጓዴንና ስማርት ሲቲን ሞዴል ያቀፈ ነው፡፡ ይህንንም በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በምንተገብረው የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ተግባራዊ እያደረግን ነው፡፡ መርሃ ግብሩ በከተማና ገጠሩ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው በማለት በመድረኩ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣይ አዘጋጅ ሆና ስለመመረጧ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሀኖይ ጉባኤ አነስተኛ ቢሆኑም በሚገባ የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚያስገኙ እና ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አሳይቷል ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡።
ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት ይሰማታል። ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን የታየውን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተባሉት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች በመመራትም የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንደስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ብሎም ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ አስፈፃሚ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ ይዘጋጃል።
ለመሆኑ ፒ4ጂ ምንድን ነው?
ፒ4ጂ ኢትዮጵያን፣ ኮሎምቢያን፣ ኬንያን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ኢንዶኔዥያን እና ቬትናምን ጨምሮ በ12 ሀገራት ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ታስቦ እ.ኤ.አ. በ2018 የተመሰረተ ባለብዙ ወገን ትብብር ነው፡፡ ዋና አላማውም በምግብ፣ ውሃ እና ኢነርጂ በትኩረት በመስራትና የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ለሰው ልጆች የተስማማች ምድርን መፍጠር ነው፡፡
ፒ4ጂ ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ ስማርት ግብርናን ይደግፋል። በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ብክነትን ለመቀነስ የሚረዱ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ያቀርባል፡፡ ታዳሽ ሃይልን ያበረታታል፡፡ የንጹህ ውሃ ተደራሽነት፣ አረንጓዴ ልማትና ወደ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ ዜሮ እንዲሆን ይሰራል፡፡ እንዲሁም ለአረንጓዴ ልማት አጋርነት በመፍጠር እ.ኤ.አ በ2030 ለማሳካት ታሳቢ የተደረጉ ዓለም አቀፍ ግቦች ዕውን እንዲሆን የሚሰራ፣ ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ዘላቂ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚተጋ ትብብር ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና የቬትናም ትብብር
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ኢትዮጵያና ቬትናም የሚያመሳስሏቸው ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው። ሁለታችንም ትልቅ እና ለሥራ የተነሳሳ ወጣት ሕዝብ ያለን፣ ለልማት እና እድገት የቆረጥን እንዲሁም በታሪካችን ሂደትም በፅናታችን የምንታወቅ ሀገራት ነን” ብለዋል።
ውይይታችን በንቁ ተሳትፎ የሚገለጥ እና ጥልቀትም የነበረው ነበር። ለጋራ እድገት እና ትብብር ያለንን ፅኑ የጋራ ተነሳሽነት አንፀባርቀናል። የሃሳብ ልውውጣችን በሁለቱ ሀገራት መካከል ለጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በር ከፍቷል ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቅርብ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት የጋራ ርዕዮታችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እና በዛሬው የዓለማችን አውድ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ይበልጥ የምናፀናበት ይሆናል ሲሉ አያይዘው ገልጸዋል።
በጊዜው አማረ