
አርባ ምንጭ
AMN – ህዳር 28/2017 ዓ.ም
አርባ ምንጭ ከተማ በቅርቡ የተመሰረተው “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ውስጥ ትገኛለች ፡፡
ከተማዋ በደቡብ ክልል የጋሞ ዞን መዲና ስትሆን ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ በ454 ኪ.ሜ ፣ ከሀዋሳ ከተማ በስተ ደቡብ በ275 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
ለኮንሶ ዞን እና ለደቡብ ኦሞ ዞን ዋና መተላለፍያ ስትሆን በቀደምት ጊዜ የአሁኑን አንጋፋውን የአየር ማረፊያን ጨምሮ የባህር ትራንስፖርት የሚሰጥባት የስልጣኔ አሻራ ያረፈባት ከተማም ናት።
ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 285 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው አርባ ምንጭ በ22 ሺህ 851 ሄክታር አስተዳደራዊና በ18 ሺህ 375 የፕላን ወሰን ላይ ከትማለች፡፡
አርባ ምንጭ 24 ዲግሬ ሰልሸስ የሙቀት መጠን ያላት ስትሆን 900 ሚሊ ሊት አመታዊ የዝናብ መጠንም አላት።
350 ሺ በላይ የሚሆኑ ህዝቦች በመከባበር በፍቅር የሚኖሩባት የፍቅር ከተማ ናት ፡፡
ህብረ ብሔራዊት ከተማዋ አርባ ምንጭ በአባያና ጫሞ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆች የተከበበች፤ የብዝሃ ህይወት መገኛ፤ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ብርቅዬ እንስሳት መናኸሪያ፤ የከተማዋ መጠሪያ የሆኑት ከአርባ በላይ ምንጮች መፍለቂያ፣ ጥቅጥቅ የደን ንጣፍ፣ የእግዜር ድልድይ፣ በኢትዮጵያ ብቸኛው የአዞ እርባታ መገኛና አስደማሚው የአዞ ገበያ ውብ የጋሞ የተፈጥሮ መልክአምድር መናገሻ፤ የሰላም ተምሳሌት ከተማ ናት፡፡
ከተማዋ ምቹ የመሠረተ ልማት፣ የሆቴል፤ የቱሪዝምና የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት አማራጭ አላት፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ የተሸፈነው አካባቢው በሰፋፊ እርሻዎች የማንጎ፤ የሙዝ፤ የአቮካዶ፤ የአፕልና የሽንኩርት ምርት ማምረቻም ናት፡፡
የአዞ ቆዳ የሚቀርብባት፤ የዓሳ ምርት ምንጭ፤ የበርካታ ቀንድ ከብት የስጋና ወተት ምርት ባለቤት የሆነችና ለኢንቨስተሩ ተመራጭ ከተማ ናት አርባምንጭ፡፡
ከተማዋ አባያና ጫሞ ሐይቅ፤ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፖርክን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መስዕቦች ባለቤት መሆኑዋ ለቱሪስት መዳረሻና ለአስተዳደር ማዕከልነት ተመራጭ ናት፡፡
አርባ ምንጭ የጋሞ ጐፋ ዞን ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች፤ በአሁን ጊዜ ህብረ ብሄራዊ ከተማ “አርባ ምንጭ” የጋሞ ዞን መዲና ሆና እያገለገለችም ትገኛለች፡፡
በአሁን ወቅትም ከ2015 ዓ፤ም ጀምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ምክትል ርዕስ መስተዳድርና የህግ አውጭ ምክር ቤት መቀመጫ ስትሆን የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር ማዕከል በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡
የአለም አቀፍ አየር ማረፍያ ፣ ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው አንጋፋው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፣ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ግዙፉ ሪፌራል ሆስፒታልን ጨምሮ በርካታ ተቋማት መገኛም ነች፡፡
አርባ ምንጭ ከተማን የማያውቋት ብዙ ሰዎች ስሟ ሲጠራ ትውስ የሚላቸው ነገር ቱሪዝም ነው፡፡
ተፈጥሮና ውበት ጥምረት ፈጥረው የሚታዩበት ከተማ ናት አርባ ምንጭ ፡፡
የስሟ መጠሪያ ከግርጌዋ ከተዘረጋው ሰፊ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የመሸጉት ብዙ ምንጮች ናቸው፡፡
የእነዚህ ምንጮች ቁጥራቸው ከአርባ በላይ እንደሚደርስም ይነገራል፡፡
ከጥቅጥቁ ደን መሽገው ለቆጣሪ ቢያስቸግሩና በየቦታው ቢንፎለፎሉ በአርባ ተወስነው ለዚህች ውብ የጐብኚዎች መዳረሻ ከተማ ስያሜ ሆኑ፡፡
እነዚህ ውብ ምንጮች ወደ ተሸሸጉበት ጥቅጥቅ ደን /ነጭ ሳር ብሔራዊ ፖርክ/ ሲያቀኑ የሚያቋርጡት ቦታ ነው፡፡
ስፍራው ለአርባ ምንጭ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ በመገኘቱ ለጐብኚዎች ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ በስፍራው ጐብኚዎች የሚኖራቸው ቆይታ ከተፈጥሮ ጋር የሚቀራረቡበት እድልን ይፈጥራል፡፡
ከጥቅጥቁ ደን መሀል አንድ ልዩ ቦታ አለ፡፡ ልዩ ስሙ የእግዜር አዳራሽ ይባላል ረጃጅም ዛፎች በእቅድ የተተከሉ ይመስል እንደ ምሰሶ በረድፍ ቆመዋል ቅርንጫፎቻቸው ደግሞ ከአናት ተቆላልፈው አንዱ በአንዱ ላይ ተኝቷል፡፡
የእግዜር አዳራሽ የሚለው ስያሜ ይህንን ውብ የተፈጥሮ ቅጥር ማንም እንዳልሰራው ለማሳየትና የራሷ የተፈጥሮ ገፀ በረከት እንደሆነ ለመግለፅ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
በእርግጥ እግዜር ካልሆነ ፍጡር እንዲህ ያለውን ውበት ከእንዲህ ያለው ደን ውስጥ በምን ተአምር ሊያበጀው ይችላል፡፡
ምንጭ፡-የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ፣ የክልሉ ማህበራዊ ትስስር ገፅ
በሽመልስ ታደሰ