የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓላት ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓት ተከብረዋል- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት ጃንሜዳን ጨምሮ በ64 ባህረ ጥምቀታት የተከበሩት የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓት ተከብረው መጠናቀቃቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታወቀ።
ሀገረ ስብከቱ ላለፉት ሶስት ቀናት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የተከበሩ በዓላትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም በሀገረ ስብከቱ በዓሉን ለማክበር ከመንበረ ክብራቸው ወተው ወደ ጥምቀተ ባህር ከሄዱ ታቦታት ውስጥ ጥር 13 የሚከበረውን ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲሁም የቅዱስ ሩፋኤልን ሳያካትት 258 ታቦታት ወደ መንበረ ክብራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ይህ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ አካላት ሀገረ ስብከቱ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በዋናነት የባህረ ጥምቀት ይዞታዎችን አስከብሮ ማረጋገጫ በመስጠት፣ ችግር ያለባቸውን ቦታው ድረስ በመሄድ ጊዜያዊ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ የጃንሜዳ የባህረ ጥምቀት መድረክ ለመስራት የሚያስፈልገውን ወጪ በመሸፈንና በፀጥታው ረገድ በጋራ በመስራት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
እንዲሁም ከደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የመንግስት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የመንግስት የፀጥታ ሀላፊዎችና አባላት ከበዓሉ ቀደም ብሎ ከነበረው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በራሄል አበበ