የአዲስ አበባ ሰማይ ደስ በሚል እና በልዩ ውበት ተሞልቷል፡፡ ፀሐይ አስደናቂ ቀለማትን በህንጻዎች ላይ ዘርታለች፡፡ አየሩ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ የከተማዋ መብራት ገና ደመቅ ብሎ መብራት አልጀመረም፡፡ ህጻናት፣ አዛውንቶች እና ወጣቶች በየካ ወረዳ 08 በሚገኘው የመዝናኛ ፓርክ ተሰባስበዋል። ምክንያታቸው ደግሞ የኪነ ጥበብ ምሽት ለመታደም ነው፡፡ ወጣት ዳግም ይልማም በዚህ መድረክ ላይ ግጥም እያነበበ ነው፡፡
….ተግዳሮት ያልጣለው ያልቆመ ከዳገት
መንገድ ነው መደመር ያከመ ስብራት
በደም የከበረች በአባቶቹ ገድል
በላቡ ያፀና በህብርና በወል
በአዲስ መሻት ለሌላ ድል
ተግባርን ያፀና ከቃል እስከ ባህል
ታሪክ አዳሽ ታሪክ ሰሪ
አሳድጎ የሰራ ሆኖ ፊትአውራሪ
አርበኛ የልማት ምንዳን አሻጋሪ
ትናንትን አድሶ ነገን ያዘጋጀ
መደመር መርህ ነው ዘመንን የዋጀ …፡፡
ወጣት ዳግም ግጥም ያቀረበበት የኪነ ጥበብ ምሽት ሀገራዊ አንድነትን፣ እህትማማችነትንና ወንድማማችነትን የማጠናከር ዓላማ ያለው ነው፡፡
በየወሩ በመዲናዋ የተለያዩ ክፍለ-ከተሞችና ወረዳዎች በወር አንድ ጊዜ የሚደረገው የኪነጥበብ ምሽት ለወጣት የጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ እድል የፈጠረ መድረክ እንደሆነ ወጣቱ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል፡፡
እንደ ሀገር ከህብረትና አንድነት አንጻር ብዙ መስራት አለብን። ወጣቶች በአብሮነት ሀገራቸውን ማስቀጠል አለባቸው፡፡ አብሮነትን መስበክ አለባቸው፡፡ ፍቅርን ማስተማር ይገባል። የእኔ ግጥም እህትማማችነትና ወንድማማችነትን፣ ወደፊት መሻገርን፣ ልማትን እና መለወጥን የሚያጎላ ነው። ሌሎች ወጣቶችም ይህን እድል ቢጠቀሙበት ብዙ ጥቅም ያገኛሉ ሲል ገልጿል፡፡
በእርግጥም የኪነ-ጥበብ ምሽቶች ለወጣት የጥበብ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች እንዲሁም መዝናናትን ምርጫ ላደረጉ ሰዎች ብዙ ፋይዳ አላቸው። ለወጣቶች እምቅ ብቃታቸውን ለመግለጥና ለማሳየት የሚያስችላቸው እድል ይፈጥራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከአንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ልምድና ትምህርት ለመቅሰም እንደሚያግዝ ወጣት ዳግም አብራርቷል፡፡
የምናቀርበው ብዙ ህዝብ ባለበት ነው። ትልልቅ ገጣሚዎችንና ሙዚቀኞችን ጨምሮ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ቦታው አረንጓዴ እና ደስ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በቅርብ በአዲስ አበባ እየተዘጋጁ ያሉት የጥበብ ምሽቶች ለመዝናናትም ሆነ ለጀማሪ ከያንያን ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ሲልም አብራርቷል፡፡
የኪነ-ጥበብ ምሽቱ አዘጋጅ አቶ አብዩ ጌታቸው በበኩላቸው ኪነ ጥበብ የወል ትርክትን ለመገንባት፣ የጋራ እውነት እና አረዳድን ለመፍጠር አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ትሩፋት በሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች የጥበብ ስራዎቹ መቅረባቸው ዝግጅቱን ልዩ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
አቶ አብዩ በአስተያየታቸው፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ይዘት አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ መከባበር እና አብሮነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የኪነ-ጥበብ ምሽቱ ብዙ ዓላማዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የጋራ ትርክትን መገንባት ነው፡፡ ሁለተኛው በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ፕሮግራሙን በማቅረብ የልማት ስራዎችን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ተተኪ የጥበብ ባለሙያ ለማፍራት ይረዳ ዘንድ ወጣቶች ከአንጋፋ አርቲስቶች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ነው፡፡
መርሃ ግብሮቹ የሚካሄዱት በህዝብ መዝናኛ እና መናፈሻ ቦታዎች ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከተጋበዙት እንግዶች በተጨማሪ በእግር የሚጓዙም ሆነ የሚዝናኑ ሰዎች እንዲታደሙ እድል ፈጥሯል በማለትም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ገጣሚ ወጣት ዳግምም በዚህ ሃሳብ ይስማማል፡፡ ባለፈው ግጥም ያቀረብኩት መገናኛ ባዶ እግር ጫማ ቤት የነበረበት አካባቢ በተሰራው መናፈሻ ነው፡፡ ስሜቱ ደስ ይላል፡፡ የሆነ የሚጨምረው ድባብ አለ፡፡ በቦታው የተገኘው ሰውም ቁጥሩ ከፍተኛ ነበር፡፡ የበለጠ አቅም ለመጨመር ጥሩ ግጥም ለመግጠም፣ ሙዚቃ ለማቅረብም ስሜትን ያነሳሳል ይላል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪች እንዲሁም ወጣቶች የግጥም ምሽቶች ላይ መታደም አለባቸው፡፡ በተለይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አንድነትን መስበክ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ያለችን አንድ ሀገር ነች፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት አብሮነትን የሚያጎሉ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ቢበራከቱ፣ ወጣቶችና ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ቢሳተፍበት መልካም ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
አቶ መስፍን ካሳም እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች መኖራቸው የሚበረታታ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ማታ ማታ በእግር መጓዝ (ወክ ማድረግ) እወዳለሁ፡፡ አረፍ ማለት የምፈልገውም አዳዲስ በተሰሩ የመናፈሻ ቦታዎች ነው፡፡ ይህ የተለመደ ተግባሬን እያከናወንኩ ሳለ ሁለት የኪነ-ጥበብ ምሽቶች አጋጥመውኛል፡፡ ለአብነትም አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አጠገብ ባለው መናፈሻ እና እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ በኮሪደር ልማት በተሰራው አዲስ መናፈሻ የኪነ-ጥበብ ምሽት ታድሜያለሁ፡፡ ግጥም አለ። ሙዚቃ አለ፡፡ ጭውውትና ድራማም ይቀርባል፡፡ ይህም ሌላ አማራጭ መዝናኛ ሆኖልኛል፡፡ እናም በቀጣይ በድንገት ሳይሆን አስቤበት እንዲህ አይነት ምሽቶችን ለመታደም ተዘጋጅቻለሁ ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አቶ አብዩ ጌታቸው በበኩላቸው መሰል የኪነ-ጥበብ ምሽቶች በቀጣይም በቋሚነት እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል፡፡ ይህ በመዲናችን ባህል እስኪሆን ድረስ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በበርካታ ሀገራትና ከተሞች የኪነ-ጥበብ ምሽቶች የተለመዱ ናቸው። በዚህ ዝግጅት ላይም ከተዝናኖት ባለፈ አብሮነትና አንድነት ቅድሚያ ይሰጠዋል። ምክንያቱም መተሳሰብና አንድነትን ለመገንባት ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ በአዲስ አበባም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአዳራሽ ውጭ በሆኑ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች ዝግጅቶችን ማቅረብ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በእነዚህ ስፍራዎች የሚቀርቡ ማለት ሙዚቃ፣ ስነ-ጽሑፍ፣ ስነ-ጥበብ፣ ቴአትር፣ ሥነ-ፅሁፍ እና ፊልም የሰዎችን ትስስር ለማጠናከር ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
አርቲስት መምህሩ ጫሞ ከዚህ ቀደም የመዲናዋን የኮሪደር ልማቶችና ኪነ-ጥበብን አስመልክቶ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባጋራው ሃሳብ፣ የኮሪደር ልማቱ ብዙ ነገር ጨምሮላታል፡፡ ሰዎች ቁጭ ብለው የሚዝናኑባቸው ቦታዎች ተሰርተዋል፡፡ በእነዚህ የመዝናኛ ቦታዎች ላይ ሰዎች ቁጭ ብለው ሙዚቃ እና ሌሎች የጥበብ ስራዎችን መታደም የሚችሉበት ሁኔታ መጨምሩ ከኪነ-ጥበብ ቱሪዝም ገቢ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ ከውጭ ለሚመጣ ጎብኝ ሳይሆን ለመዲናዋ ነዋሪዎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙዚቃዎች በእነዚህ ቦታዎች ቢቀርቡ የእርስ በእርስ ትስስር ይጨምራል፣ ገቢ ያድጋል፡፡ የሰዎች አስተሳሰብና የመረዳዳት ባህል ከፍ ይላል በማለት አብራርቷል፡፡
አርቲስቱ አክሎም ኪነ-ጥበብ ያቀራርባል፤ ያስተዋውቃል፤ አብሮነትን ያጠናክራል፡፡ ገቢ ያመጣል፡፡ ስለዚህ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ማሳደግ ይገባል ሲል ሃሳቡን አጋርቷል፡፡
በጊዜው አማረ