የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የትብብር አቅም እየፈጠረ ነው

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል /ሮክ/ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የአገራትን የትብብር አቅም እየፈጠረ መሆኑን የዩጋንዳ እና ኬንያ የፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች ገለጹ፡፡

የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል /ሮክ/ አባል ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ስልት የሚቀይሱበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩጋንዳ ፖሊስ ሰራዊት ከፍተኛ ኮሚሽነር ኦብዎና ጆሴፍ፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የተለያዩ አገራትን ስለሚያቋርጡ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ሽብርተኝነትና ሌሎችም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የአገራት ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ወንጀሉን ለመከላከል ኢንተር ፖል፣ አፍሪፖልና ሌሎችም ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ተቋማት ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል /ሮክ/ በቀጣናው ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል /ሮክ/ ስብሰባ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የአገራትን የትብብር አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት የወንጀል ምርመራ እና የኢንተርፖል ብሔራዊ ማዕከላዊ ቢሮ ዳይሬክተር ኢብራሂም ጅሎ፤ በበኩላቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የትብብር ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል፡፡

የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል እና መሰል ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ የወንጀል መከላከል ተቋማት ውስብስብ ወንጀሎችን ከመፍታት ባለፈ የአገራትን የወንጀል ምርምራና የክስ ሂደት የተቀላጠፈ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው የካርቱም ቀጣናዊ ትብብር ማዕከል ጉባኤ በቀጣናው ሀገራት መካከል ትብብርን በመፍጠር የመከላከል አቅምን ያሳድጋል ነው ያሉት የፖሊስ መኮንኖቹ።

በመሆኑም በድንበር አካባቢ የጸጥታ ቁጥጥሩን በማሳደግ በቀጣናው የሚስተዋለውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።

በትናንትናው እለት በተካሄደው የስብሰባው የመክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

All reactions:

3535

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review