የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ካርኒ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሺንግተን ሊገናኙ ነው።
የ60 ዓመቱ የሊበራል ፓርቲ መሪ፣ ከአሜሪካ ጋር ያሉ ሁኔታዎች በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር እንደ ቀድሞ እንዳይደሉ እና በዚህ ስብሰባም በፍጥነት ስምምነት ላይ ሊደረስ የሚችል ነገር ይኖራል ብሎ ማንም እንዳይጠብቅ አስጠንቅቀዋል፡፡
ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ካናዳ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንድትሆን በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ የነበሩት ትራምፕ፣ የአሜሪካ ዋነኛ ሸሪክ እና የንግድ አጋር በሆነችው ካናዳ ላይ ከፍ ያለ ታሪፍ በመጣል የንግድ ጦርነትም አጭረውባታል፡፡
ታሪፍን ለመቋቋም እና ሰሜናዊ ጎረቤትን የማጠቃለል ዛቻን በፅኑ ለመታገል ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሏል፡፡
ትራምፕ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባለፈው ሳምንት ከተነጋገሩ በኋላ፣ ካርኒን “በጣም ጥሩ ሰው” ያሉ ሲሆን፣ በትናንትናው ዕለት ግን ካርኒ ስለምን ጉዳይ ሊያወሯቸው እንደፈለጉ እንደማያውቁ መናገራቸውን አር ቲ ኢ ዘግቧል፡፡
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ካርኒ በዳግም ምርጫው ካሸነፉ በኋላ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ሲያገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በታምራት ቢሻው