2ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሳምንት የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ተከፍቷል፡፡
በ2ኛው የኮሜሳ ሳምንት ከተያዙ መርሃ ግብሮች መካከል አንደኛው የሆነው የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ ዛሬ የተከፈተ ሲሆን፥ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ የኮሜሳ ሴት ነጋዴዎች ባዛርና አውደ ርዕይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚሁ የኮሜሳ ሳምንት የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የኮሪደርና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን የመጎብኘት መርሃ ግብር መያዙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ጥምረቶች ላይ ስታደርጋቸው የነበሩ ድርድሮች ውጤታማ እንዳልነበሩ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ከለውጡ በኋላ ይህን ለመቀየር በርካታ ስራዎችን ስትሰራ መቆየቷንና አሁን ላይ በሙሉ አቅሟ መስራት እንደጀመረች ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባስመዘገበቻቸው ዘርፈ ብዙ ስኬቶች 21 ሀገራትን በአባልነት የያዘውን የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሳምንት የንቅናቄ መድረክን እንድታዘጋጅ መመረጧም ተገልጿል።
በበላይሁን ፍሰሀ