• የኮሪደር ልማቱ የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ይዞላት በመጣው በረከት እንደ ንስር ራሷን እያደሰች የውበት ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የበርካቶችን ቀልብ ገዝታለች፤ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጉባኤዎችም አዘጋጅታለች፡፡ አሁንም የበለጠ ለመድመቅ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ምዕራፍ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶችም ወደ መጠናቀቁ እየተቃረቡ ነው፡፡ የተጠናቀቁም አሉ፤ ለአብነትም በቅርቡ ተመርቆ ወደ ተሟላ አገልግሎት የገባውን የካዛንቺሱን መስመር መጥቀስ ይቻላል፡፡
ካዛንቺስ ትልልቅ ሆቴሎች የሚገኙበት፣ በበርካታ ቱሪስቶች እና ዲፕሎማቶች የሚዘወተር እንደመሆኑ በአካባቢው የተሰራው የኮሪደር ልማት ከፍ ያለ ትርጉም እንዳለው በአካባቢው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፣ የሆቴል አስተዳዳሪዎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የቱሪዝም ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ የቀድሞው የካዛንቺስ ግጽታ እምብዛም ሳቢ እንዳልነበር የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አካባቢው ደሳሳ ቤቶች የሚበዙበት፣ አሰፋፈሩም በዘፈቀደ የሆነ፣ መጸዳጃ ቤትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቅር የሚያሰኝ እንደነበርም በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡
በአካባቢው የተከናወነው የኮሪደር ልማት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ በረከት ይዞ የመጣ ስለመሆኑ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሩም ዲቪዥን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታየ በሰጡን አስተያየት ጠቁመዋል፡፡ አክለውም፣ “ካዛንቺስ ከሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች በተለየ በርካታ ትልልቅ ሆቴሎች የሚገኙበትና የከተማዋ እንብርት ቢሆንም ዙሪያው በደሳሳ ቤቶች የተከበበና ለእይታም ሳቢ አልነበረም፤ የኮሪደር ልማቱ ከመሰራቱ በፊት መፀዳጃ ቤትን ጨምሮ ለነዋሪዎችም፣ ለጎብኚዎችም ሆነ ለስራም የማይመች ነበር፡፡” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የአካባቢውን ገፅታ መቀየር ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች ምቾች የሚሰጥ፣ የጎብኝዎችንም ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም ሌላ ለቱሪዝም በተለይም ለሆቴል ኢንዱስትሪው ትልቅ በረከት ይዞ መምጣቱን ነው የነገሩን፡፡
ለ20 ዓመታት በማስጎብኘት ስራ ላይ የተሰማሩት የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ጌታሰው ልሳነወርቅ በበኩላቸው፣ በከተማዋም ሆነ እንደሀገር እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለቱሪዝሙ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
በካዛንቺስ አካባቢ የተከናወነው መሠል ስራ ደግሞ ትርጉሙ ጥልቅ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ የካዛንቺሱ የኮሪደር ልማት የአስፓልት፣ የእግረኞችና የብስክሌት መንገዶችን፣ የሕፃናት መጫወቻዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን፣ የሕዝብ ፕላዛዎችን፣ አረንጓዴ ፓርኮችን፣ የሕዝብ መጸዳጃዎችን፣ ሱቆችን እና የመኪና ማቆሚያዎችን ያካተተው ነው፡፡
በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ እይታ ዋጋ እንዳለው ያወሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ የአካባቢ ገፅታ ውብና ማራኪ ሲሆን ከገበያ አኳያ የዋጋ ልዩነት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ እይታ ይሸጣል ብለው፣ ብዙውን ጊዜ እንግዶች ጥሩና ሳቢ እይታን ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ የኮሪደር ልማት የተመልካችን ቀልብ የሚስብ ብሎም ለሆቴል ኢንዱስትሪው ከፍተኛ መነቃቃትን ይዞ የመጣ ነው ብለዋል፡፡
ካዛንቺስ መሃል ከተማ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ለታላቁ ቤተ መንግስት፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ ሳይንስ ሙዚየምና ለተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ቅርብ በመሆኑ እንግዶች በእግራቸው ተንቀሳቅሰው ለመጎብኘት የኮሪደር ልማቱ በእጅጉ ይጋብዛል ብለው፣ በዚህም በዐይናቸው ሳቢ ነገሮችን ከመመልከት በተጨማሪ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር እንደሚያገኙም ጠቁመዋል፡፡
የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ጌታሰው፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ ህብረት፣ የበርካታ ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ በሁሉም አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡ በቱሪዝም ደረጃ ከፍ ካሉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያ ተጠቃሽ መሆኗን አስታውሰው፣ በርካታ የውጪ ዜጎች ለጉብኝት ኢትዮጵያን እንደሚመርጡ ሆኖም ግን ቀደም ባሉት ዓመታት የሚመጡ ጎብኚዎች አዲስ አበባ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዷላት ቅሬታ ያነሱ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡
እንደ አቶ ጌታሰው አስተያየት፣ ጎብኚዎች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል የከተማ ፅዳትና ውብት መጓደል፣ በእግር ለመንቀሳቀስ የሚመች መንገድና በቂ የመዝኛና ስፍራዎች አለመኖር፣ በቂ የቴሌኮም ኔትዎርክ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህንና መሠል ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ የኮሪደር ልማቱ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደልም፡፡
በአዲስ አበባ ካዛንቺስ በሚገኘው የንግድ ሱቃቸው ውስጥ አግኝተን ያነጋገርናቸው አቶ ሰለሞን ጌትዬ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የበርካታ ኤንባሲዎችና ዲፕሎማቶች መቀመጫ ብትሆንም የሰለጠነ የከተሜነት ገፅታ አሟልታ የያዘች አልነበረችም ብለዋል፡፡ አክለውም፣ በተለይ ካዛንቺስ ትልልቅ ሆቴሎች የሚገኙበት እንደመሆኑ በርካታ እንግዶች የሚመላለሱበት ቢሆንም ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች፣ መንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አለመኖራቸው የሀገርን ገፅታ የሚያጎድፍ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የአካባቢውን ገፅታ የአሻሻለና ከተማዋን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርጋት ነው ብለው፤ የመብራት፣ የውሃና ቴሌኮም መሰረተ ልማት በከፍተኛ ቅንጅት መከናወኑ ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ውብና አረንጓዴ በማድረግ ለኑሮ ተስማሚና ለጎብኝዎችም ማራኪ አድርገዋታል ባይ ናቸው፡፡
በተለይ እርሳቸው የእለት ስራቸውን በሚያከናውኑበት ካዛንቺስ በኮሪደር ልማቱ በሁለቱም የመንገድ ዳርቻዎች ለእግረኛ ምቹና ለአደጋ የማያጋልጡ መንገዶች መገንባታቸው አካባቢውን ውብ ገፅታ ከማላበስ ባለፈ የስራ አካባቢያቸውን እንዲወዱና ስራቸውን በትጋት ለመስራት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
በተለያየ አጋጠሚ ለስራና ጉብኝት ወደ ውጭ ሀገራት ሲሄዱ የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ በተለያዩ አትክልቶችና አበቦች ያማሩ ማራኪ ቦታዎችን መመልከታቸውን ጠቁመው፣ በሀገራችንም ተፈጥሮ የለገሰችንን ምቹ አየርና የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ሰፊ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች መሰራታቸው በእጅጉ እንደሚደገፉ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ በተጨናነቀ አኳኋን የሚኖርባቸው አካባቢዎች የመንገድ አካፋዮችና ዳርቻዎችን ማልማት ምቹ የመኖሪያና የስራ ከባቢን ለመፍጠር ያስችላል ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንሚገባም ተናግረዋል። የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት በመንገድ አካፋይና ዳርቻዎች የተተከሉ የጥላና የውበት ዛፎች እንዲሁም መናፈሻዎች አካቶ መያዙ ለከተማዋ ውበትም ሆነ ለዜጋው ምቾትን የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ካዛንቺስ በሚገኝ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ሲዝናኑ ያገኘናቸው አቶ ፈድሉ ከድር በከተማዋ የተከናወነውና እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ከተጨናነቀና ንፁህ ካልሆነ አየር ወጥታ ተስማሚና ውብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በተለይ በካዛንቺስ የነበሩት የአካባቢውን ገፅታ ያበላሹ አሮጌ ቤቶች አሁን የሉም፤ ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ ምቾት የማይሰጡ ጠባብ መንገዶችም እንዲሁ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ ሰፋ ብለው መሰራታቸው እግረኛ መንገድ ባለፈ የእግር ጉዞ ለማድረግም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል የሚል አስተያየት አጋርተውናል፡፡
ዘመናዊና አዳዲስ የመንገድ መብራቶችም አካባቢውን ልዩ ገፅታ በማላበስ ከተማዋን ውብና ለኑሮ ተስማሚ እያደረጉ ነው፡፡ ይህም ብዙሃኑ ለሚጠቀምበትና ተስማሚ የጋራ ከተማ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን በጉልህ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አክበረት ገብረኪዳን የተባሉ ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን የማይመጥኑ ያረጁና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን ከማስተካከል በተጨማሪ የጠበቡ መንገዶችን በማስፋት እና የመንገድ አካፋዮችን አረንጓዴ በማልበስ ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በካዛንቺስ ኮሪደር ልማት ምረቃ ወቅት የካዛንቺስ መልሶ ማልማት በአገልግሎትም በእኩል ተጠቃሚነትም ኅብረተሰብን እንዲያገለግል የተቀረፀ መሆኑን ነው የገለፁት። የመጀመሪያው ምዕራፍ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት መጠናቀቅን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በመልሶ ግንባታ ውስጥ ካሉ ስምንት ዐበይት ኮሪደሮች አንዱ የካዛንቺስ አካባቢ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፣ በአንድ ወቅት ከተዘነጉ የማዕከላዊ አዲስ አበባ ስፍራዎች አንዱ የሆነው ካዛንቺስ አካታች እና ተደራሽነቱ የተስፋፋ ሕዝባዊ ስፍራ እንዲሆን በአዲስ ምናብ መቃኘቱን አመልክተዋል። “በአስደናቂ ሁኔታ በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀው የካዛንቺስ ለውጥ ለዘመነ ከተማ ልማት ሥራችን ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት መሠረት የሚጥል ነው” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ በካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ ላይ ሀገር የማበልፀግ ራዕያችንን በመጋራት በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን፣ እረፍት አልባ የስራ መርሃ ግብር በማሳለፍ አብረዋቸው የሰሩ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ አመራሮች፣ ሰራተኞች እና ተቋማትን ማመስገናቸው ይታወሳል፡፡
የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት አንዱ አካል የሆነውን የሴቶች አደባባይ የሴቶችን አጠቃላይ ሚና እና በትውልድ ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ትልቅ ድርሻ በሚያጎላ መንገድ ተገንብቶ መመረቁንም ከንቲባዋ ጠቅሰዋል፡፡ አደባባዩ ስያሜውን ካገኘ ቆየት ያለ ቢሆንም፤ የሴቶችን ሚና ሊያሳይ የሚችል ምንም የተለየ መገለጫ ያልነበረውና አካባቢው ለዐይን ብዙም የማይመች የነበረ ሲሆን፤ በካዛንቺስ መልሶ ማልማት ስራ ግን ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በሚገልፅ መልኩ ተገንብቷል። በሴቶች አደባባይ ዙሪያ 105 ሱቆች የተገነቡ ሲሆን፣ በእነዚህ ውስጥም 90 በመቶ የስራ እድል ያገኙት ከመፍረሱ በፊት እዚያው ንግድ የነበራቸው ወገኖች መሆናቸውን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአካባቢው ላይ ከተለያዩ አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ አውጥተን፣ አሰልጥነን ለስራ ያበቃናቸው ከ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፅጊያ ማዕከል የተመረቁ ሴቶች የሚሰሩባቸው ፀጉር ቤት፣ ካፍቴሪያ፣ ሬስቶራንት፣ የልብስ ስፌት፣ ስጋ ቤት እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችንን በመንከባከብ ገቢ የሚያገኙባቸው ናቸው። ሌሎቹ አብዛኛዎቹ ሱቆች በአካባቢው ይነግዱ የነበሩና ስራቸውን እዚያው በተለመደው ስፍራ እንዲቀጥሉ የተደረጉ ነጋዴዎች የሚሰሩባቸው ናቸው ብለዋል።
የካዛንቺስ ኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ 1 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ 40 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 81 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 20 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የብስክሌት፣ 15 የህጻናት መጫዎቻ ቦታዎች፣ 5 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ 16 የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች እና አረንጓዴ ፓርኮች፣ 19 የመጸዳጃ ቤቶች፣ 105 የንግድ ሱቆች፣ 40 የመኪና ማቆሚያዎች እና ተርሚናሎች ተካትተው መገንባታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጸህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በሽዋርካብሽ ቦጋለ