የኮፕ 29 ጉባኤ አወዛጋቢ ውሳኔ ተቃውሞ አጭሯል

AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም

በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ለ12 ቀናት የተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታዳጊ ሀገራት ከሚያስፈልጋቸው የፋይናንስ ድጋፍ እጅግ ያነሰ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተቃውሞን አስነስቷል፡፡

የዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዋና ዓላማ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና ወደ ታዳሽ ሀይል ምርት ለሚደረገው ሽግግር የሚሆን በቂ የፋይናንስ በጀት መመደብ ነው፡፡

በተለይም በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው የካርበን ልቀት የሚያመነጩ በመሆናቸው ታዳጊ ሀገራትን ተጎጂ አድርጓል፡፡

ታዳጊ ሀገራትም ይበልጥ ተጎጂና ለአየር ንበረት ለውጥ ቀውስ ተጋላጭ በመሆናቸው በትሪሊዮን ቤት የሚቆጠር የፈይናንስ በጀት ከበለጸጉት ሀገራት በየዓመቱ እንዲበጀት በጉባኤው ሲከራከሩ ሰንብተዋል፡፡

የበለጸጉት ሀገራት በበኩላቸው ሊደረግ በሚገባው የፋይናንስ መጠን ላይ መስማማት ካለመቻላቸውም በላይ ከስምምነት ላይ የሚደርሱት የበጀት ድጋፍም ቢሆን በየወቅቱ የት እንደደረሰ ክትትል ሊደረግበት ይገባል የሚል አቋምን አንጸባርቀዋል፡፡

የኮፕ 29ኙ ጉበኤ 300 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ላይ ከስምምነት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ በታዳጊ ሀገራት ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በጉባኤው ተወሰነው የ300 ቢሊዮን ዶላር በጀት ከታዳጊ ሀገራት አስተያየት በፊት በፍጥነት ውሳኔ እንዲያገኝ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በጉባኤው የታደሙት የናይጀሪያ እና ህንድ ተወካዮች ውሳኔውን “ስድብና ቀልድ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ውሳኔው ተቀባይነት የሌለው እና ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤ “ይህ እንደቀላል የምንመለከተው እና እጅ አጨብጭበን የምንለያይበት ጉዳይ አይደለም” ማለታቸውን የቢቢሲ እና አፍሪካ ኒውስ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review