“የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማት የከተማዋን እስትንፋስ ማስቀጠል ነው”

You are currently viewing  “የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማት የከተማዋን እስትንፋስ ማስቀጠል ነው”

          የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ወ/ጊዮርጊስ

“ቤና . . . ቤና እንዴብና፣

ማሊፍ ጉጉበና፣

ኦፍ ቀበኔ ፈና፣

ኤሳ? . . . ቢሻን ቀበና. . .”

እያለ ነው ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ “ቀበና” የሚለውን ዜማ በአፋን ኦሮሞ የሚጀምረው፡፡ ትርጉሙም፡-  

“ተነሱ . . . እንጓዝ፣ እንሂድ፣

ለምን እንቃጠላለን፣

ቀበና ወንዝ ወርደን ቀዝቀዝ እንበል!”

የሚል መልዕክት አለው፡፡ “ደራሽ ውሃ ከላይ ከእንጦጦ ድልድይ ላይ፤ አጎዛን ተሻግሮ ተባለ ቡልቡላ” እያለ የወንዙን ምንጭና በተለያዩ ቦታዎች ያለውን ስያሜ ያነሳል፡፡ የቀበና ወንዝ ከእንጦጦ ፈልቆ ተራራማና ውብ በሆነው መልክዓምድር መካከል ባለው ሸለቆ በርካታ ሰፈሮችን እያቆራረጠ እስከ አቃቂ ድረስ ይፈሳል። ቀበና ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መዝናኛን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች ሲሰጥ የቆየ፣ የብዙዎች ታሪክና ትዝታ የታተመበት እንደሆነ ድምፃዊው በዜማው ያነሳሳል፡፡

አቶ ደበበ ሀይሉ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ በተለምዶ “ሰፈረ ሰላም” በሚባለው አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ የቀበና ወንዝ “ድሮ በክረምት ወቅት ዝናብ ከዘነበ ማንም የሚሻገረው አልነበረም፤ በጣም ሀይለኛ ነበር፡፡ ከተፈጥሯዊ መፋሰሻው እየወጣ ይሄድ ነበር፡፡” ሲሉ የወንዙን ባህርይ ያነሳሉ፡፡

“በልጅነቴ ከብት እየጠበቅኩ ውሃ ሲጠማኝ በደረቴ ተኝቼ ነበር የምጠጣው፤ በጣም ንፁህ ነበር፡፡ ልብስም የምናጥበው ወንዙ ዳርቻ ላይ ነበር፡፡ ወደ ወንዙ የሚገባው ገባር የሆነው ባላንጎ ወንዝም ንጹህ ነበር፡፡ እንደውም ተጠልፎ ለአትክልት ልማት ሲውል አውቃለሁ።” ሲሉ አቶ ደበበ የሚያስታውሱትን አጋርተውናል፡፡

በልጅነታቸው ወደ አካባቢው እየመጡ እንጨት መልቀም፣ የውሃ ዋና እና የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወት ማሳለፋቸውን የሚያስታውሱት የፈረንሳይ ኬላ አካባቢ ነዋሪው አቶ ሰለሞን ሀይሉ፣ ከዓመታት በኋላ ግን ወደ አካባቢው መምጣት አቁመው ነበር። ምክንያቱም ደግሞ ወንዙና የወንዙ ዳርቻ በከፍተኛ ደረጃ በመበከሉ፤ የወንዙ ተፈጥሯዊ መልክ እየተቀየረ በመምጣቱ ነበር፡፡

ወንዙ ከመበከሉ ባሻገር በተለይ በክረምት ወቅት የሚከሰተው ጎርፍ የሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያስከትል እንደነበር አቶ ሰለሞን ያስታውሳሉ፡፡ በአንድ ወቅትም የ16 ዓመት ልጅ እያሉ ከጓደኞቻቸው ጋር እየዋኙ እያለ ድንገተኛ ጎርፍ ተከስቶ፤ ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡበትና እሳቸው ከሞት የተረፉበትን አጋጣሚ አይረሱትም፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ ባለው የቀበና ወንዝ አካባቢ የኖሩት አቶ ፈይሳ ኡርጌቻ፣ የቀበና ወንዝ በድሮ ጊዜ ንፁህ፣ ለመጠጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲውል የቆየ ቢሆንም በጊዜ ሂደት እየቆሸሸ መጥቷል፡፡ ከላይ ሲታይ ንጹህ ይምሰል እንጂ ውስጡ በሽታ አምጪ በሆኑ የተለያዩ ኬሚካልና ፍሳሾች ተበክሎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ልማቱ እያመጣ ያለው ለውጥ

አዲስ አበባ ከተማ ከ76 በላይ ወንዞች አሏት፡፡ እነዚህ ወንዞች በድሮው ጊዜ ተፈጥሯዊ መልክና ይዘታቸው ሳይቀየር ለህብረተሰቡ የተለያየ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የከተማዋ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣት ጋር ተያይዞ በርካታ ነዋሪዎች በህጋዊና አብዛኞቹ በህገ ወጥ መንገድ በወንዝ ዳርቻዎች ሰፍረዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችም ወንዞችን ተከትሎ የተገነቡ በመሆኑ ወንዞች ለከፍተኛ ብክለት ተዳርገዋል። የወንዞቹ ስነ ምህዳርና ብዝሃ ሕይወት ሀብት ተመናምኗል፡፡ በዚህም ምክንያት የውበትና የመዝናኛ

ስፍራ ከመሆን ይልቅ ሰው ለማየት የሚጠየፋቸው፣ የቆሻሻ መጣያ፣ የጎርፍና የጤና ስጋት ምንጭ ሆነው እንደቆዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ወ/ጊዮርጊስ ለዝግጅት ክፍላችን ያስረዳሉ፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ለዘመናት ተረስተው የቆዩት ወንዞችን ለማልማት፣ የተጎሳቆለውን ገፅታቸውን ለመቀየር፣ ከብክለት ለመታደግ የከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከተያዙና ግንባታቸው በፍጥነት እየተከናወኑ ከሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች መካከል 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ይጠቀሳል፡፡ 

አቶ አሰግደው እንደሚገልፁት፤ በቀበና ወንዝም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ገፅታ በመቀየርና የአካባቢ ጥበቃን በመጠበቅ በኩል ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 44 ላይ እንደተቀመጠው ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ልማቱ ይህንን ይመልሳል፡፡ ዜጎች ጤናቸውን እንዲጠብቁ፣ ንፁህና አረንጓዴ አካባቢ እንዲኖሩ ብሎም የመዝናኛ አማራጭ፣ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ጎርፍን በመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው እንደሆነ አቶ አሰግደው ያነሳሉ። በከተማዋ በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር የከተማ አስተዳደሩንና ነዋሪዎችን ከሚያስጨንቁ አደጋዎች መካከል ጎርፍ አንዱ ነው፡፡ በርካታ ዜጎችም በወንዝ ዳርቻ፣ የቤታቸውን ግርግዳ ወንዙ ስር በማድረግ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋዎች ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ በወንዝ ዳርቻ ልማት ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ነዋሪዎችን በማንሳትና ንፁህና ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረግ፣ የጎርፍ መከላከያ የድጋፍ ግንቦችን በመገንባት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የጎርፍ አደጋ ስጋትን መከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠር ተችሏል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የወንዞች ብክለትን በመከላከልና ስነ ምህዳርና ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው አቶ አሰግደው ያነሳሉ፡፡ አብዛኞቹ ከመኖሪያ ቤትና ተቋማት የሚወጡ ፍሳሾች ወደ ወንዞች ነበር የሚለቀቁት፡፡ ልማቱ ወደ ወንዞች የሚለቀቀውን ፍሳሽና ደረቅ በማስቀረት

ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ የወንዝ የብክለት መነሻ አካባቢዎችን ከማልማት አኳያም በቀበና ወንዝ ተፋሰስ አንቆርጫ አካባቢ ያለው በሁለተኛ ምዕራፍ ተይዞ እንደሚለማ ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ አሰግደው እንደተናገሩት፣ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት የመዝናኛ፣ የእግረኛና ሳይክል መንገድ፣ የልጆችን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን አካትቶ እየተገነባ እንደሚገኝ አንስተዋል። “የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማታችን ገፅታን ከመቀየር ባሻገር የከተማዋን ሕይወት እስትንፋስ ማስቀጠል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ወንዞች በአግባቡ ባለመያዛቸው የከተማውን ገፅታ አበላሽተዋል፣ የጤና ስጋትም ነበሩ፡፡ በኢኮኖሚ ከተማዋ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አጥታለች፡፡ ወጣቶችም በመዝናኛ አልነበራቸውም። ወንዞቹ ሲለሙ እነዚህን ሁሉ ጥቅሞች ያስገኛሉ” ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት አካል የሆነው ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ እስከ ቤላ ድልድይ ያለው ልማት ተጠናቅቋል፡፡ ይህንን አካባቢ በአካል እንደተመለከትነው ልዩ መልክዓምድራዊ ገፅታን የተላበሰ ነው። ነፋሻማ አየር፣ ከአዕዋፋት ዜማ ውጪ ሌላ የማይሰማበት ፀጥታው፣ በኮንክሪት የተሰሩ ረጃጅምና ውብ የእግረኛ መንገዶች፣ አበቦች፣ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችና አዕዋፋት፣ ሳር ልዩ ሀሴትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ከአንዱ የተራራ ጫፍ ወደ ሌላው ለመሸጋገርና ለመዝናናት የሚያስችለው ከርቀት ሲታይ አረንጓዴ ገመድ የሚመስለው ረጅም ተንጠልጣይ የሽቦ ድልድይም ሌላው አስደናቂ ስራ እንደሆነ አይተናል፡፡

በቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት የኮንሶዎች አሻራ ይታያል፡፡ ኮንሶዎች በዓለም የታወቁበት የእርከን ስራ ጥበብ ተገልጧል፡፡ በተለይ ደግሞ የወንዙ ዳርቻና አካባቢው በውሃ እንዳይሸረሸር ድንጋዮችን በጥልፍልፍ የብረት ሽቦ (ጋቢዮን) በማሰር በሚያምር ሁኔታ የተሰራውንም ማየት ችለናል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በወንዝ ዳርቻ ልማቱ አካባቢያቸው በመቀየሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ “አሁን ወንዙ ፀድቶ አካባቢያችን ተቀይሯል። ውብ የሆኑ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች ተተክለው በማንኛውም ጊዜ የምንዝናናበት፤ እዕምሯችንን የምናድስበት፤ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለከተማዋና ለሀገር የሚተርፍ ስፍራ ሆኗል፡፡” ሲሉ ነው አቶ ፈይሳ የገለፁት፡፡  

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review