የዓለምን 1.5 ትሪሊዮን ዛፎች የሚያጠና አዲስ ሳተላይት ወደ ሕዋ ተላከ

You are currently viewing የዓለምን 1.5 ትሪሊዮን ዛፎች የሚያጠና አዲስ ሳተላይት ወደ ሕዋ ተላከ

AMN – ሚያዚያ 24/2017 ዓ.ም

ባዮማስ የተባለው በአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ የተላከው ይህ አዲስ የሳተላይት ተልእኮ ደኖች ካርቦን እንዴት እንደሚወስዱ ለመረዳት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ወሳኝ የሆነውን የመጀመሪያ ዝርዝር አለም አቀፍ የደን ባዮማስ ካርታ መፍጠርን ያለመ ነው።

እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 29 ቀን 2025 የተወነጨፈው ሳተላይቱ በደቡብ አሜሪካ ሰሜን ምስራቅ ባህር ዳርቻ ከሚገኘው የፈረንሳይ ግዛት አካል ፍሬንች ጎያና የጠፈር ማዕከል መነሳቱ ተነግሯል።

40 ጫማ ርዝመት ያለው አንቴና ተሸክሞ ከሚያጠናቸው ደኖች አንዱ በሆነው አማዞን አናት ላይ የበረረው ሳተላይቱ ከደኖች አናት በታች የተደበቁ ቅርጫፎች እና ግንዶች ምን እንደያዙ በጥልቀት ለመመልከት የሚያስችለውን ፒ-ባንድ ራዳር የተሰኘ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል።

የራዳር መረጃው የሳይንስ ባለሞያዎቹ ደኖችን እንዲመዝኑ እና ምን ያህል ካርቦን እንደሚያከማቹ ለማወቅ የሚረዳቸው ሲሆን በተለይም ርቀው በሚገኙ ሞቃታማ አካባቢዎች ያለውን የመረጃ እጥረት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታል ሲል ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል።

ተልእኮው ለአምስት ዓመታት በየቀኑ ከ15-16 ጊዜ ምድርን የሚዞር ሲሆን መጀመሪያ በሞቃታማ ደኖች ላይ እንደሚያተኩር ተመላክቷል።

ተልዕኮውን የመሩት እንደ ሾን ኩዌን ያሉ ሳይንቲስቶች የአየር ንብረት ለውጥ እና የደን መጨፍጨፍ የደን የካርበን ማከማቻዎችን እንዴት እንደሚቀይሩ ለመከታተል ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል ።

ተልእኮው እንደ የናሳው GEDI እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ የተመሰረተ የዛፍ ካርታ ስራን የመሳሰሉ ሌሎች የደን ክትትል ጥረቶችን የሚያግዝ ሲሆን ጠለቅ ያለ ግንዛቤዎችን ይሰጣል ተብሎለታል።

ከተልእኮው የሚገኙ መረጃዎች በአንድ አመት ውስጥ ይፋ ይደረጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review