AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም
የዓድዋ ድል የአፍሪካን መጻኢ እድል የቀረጸ፣ የተባበረች እና የበለጸገች አፍሪካን ለመመስረት መሰረት የጣለ መሆኑን ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት ተናገሩ።
” ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ በሚገኘው 129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙት ሊቀመንበሩ ዓድዋ ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫ፣ የህዝቦች ክብር የተረጋገጠበት ፣ አፍሪካ ከውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆና የመኖር መብት እንዳላት ለአለም ህዝብ ያረጋገጠ ታላቅ ድል ነው ብለውታል።

የአፍሪካ ህብረት የ2025 መሪ ቃል ማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የሚል መሆኑን ያስታወሱት ሙሳ ፋኪ መሀመት አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት እና በዘረኝነት መንፈስ ለደረሰብን ግፍ ሁሉ ፍትህንና ካሳን እየጠየቅን እንገኛለን የዓድዋ ድል ደግሞ ለዚህ ጥያቄያችን የመንፈስ ስንቅ ይሆነናል ነው ያሉት።
ከአፍሪካ ውጭ በሌላው አለም የሚኖሩ አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች አፍሪካ ፍትህና ካሳን እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉም ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዓድዋን ስናከብር በወቅቱ የነበረውን የአይበገሬነት እና ለወራሪ እጅ ያለመስጠት መንፈስ ዳግም በውስጣችን እንዲፈጠር ያስችለናል ያሉት ሙሳ ፋኪ መሀመት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የመላው አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች ኩራት ናችሁ ብለዋል።
በሰብስቤ ባዩ