AMN- የካቲት 23/2017 ዓ.ም
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ቅኝ ለመግዛት በመጣ በጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ በዓድዋ የተቀዳጀችው ታሪካዊ ድል የፓን አፍሪካኒዝም የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል።
ቅኝ ገዥነት በመቃወምም ለአፍሪካ አንድነት የሚደረገውን ትግል አነሳስቷል።
በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በንግሥት ጣይቱ ብጡል መሪነት እና በአይበገሬ የጦር ሹማምንቶች ፊታውራሪነት የሀገሬውን ህዝብ በነቂስ አስተባብሮ የተካሄደው ወሳኙ ጦርነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ በአህጉሪቱ የፀረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠል አድርጓል።
የዓድዋ ድል በዘመኑ አንድ አፍሪካዊ ሀገር የአውሮፓን የአይነኬነት አስተሳሰብ የደመሰሰ አስደማሚ ድል ነው።
ይህ ድል መላ አፍሪካ እና ትውልደ አፍሪካውያን ወደ ንቅናቄ ያስገባ ሲሆን፣ ይህም በግንባር ቀደምትነት ፊት መሪ የሆኑ የነፃነት ታጋዮች እና ምሁራን ፍላጎትን አቀጣጥሏል።
ማርከስ ጋርቬይ እና ክዋሜ ንክሩማህን ጨምሮ ታዋቂ የፓን አፍሪካኒዝም መሪዎች አድዋ ለአፍሪካ ወራሪን የመመከት እና እራስን የማስከበር ተምሳሌት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ።
ድሉ የፓን አፍሪካ ጉባዔዎች እንዲመሰረቱም ምክንያት ሆኗል።

ይህም ለአፍሪካ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ እና በስተመጨረሻም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ኦኤዩ) ለአሁኑ የአፍሪካ ህብረት (ኤዩ) ምሥረታ መሠረት ጥሏል።
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም የተጫወተችው ተምሳሌታዊ ሚናም ቀጥሎ በፈረንጆቹ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ኦኤዩ) ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫው በአዲስ አበባ እንዲሆን አስችሏል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን የነጻነት ቀንዲል አድርገው ይመለከቷታል።
የአድዋ ድልም የቅኝ አገዛዝን በራስ ትግል የማክሸፍ ወኔ እና የኩራት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ እና የተቀረው የአፍሪካ ክፍል የአድዋ ድል በዓልን ሲያከብሩ፣ የጦርነቱን ጥልቅ ትርጉም አጉልተው ይገልጻሉ።
ምሁራን እና የታሪክ ተመራማሪዎችም “ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ድል ነው ” ይላሉ።
የዓድዋ ድል፡ አንድነት፣ ስልታዊ አካሄድ እና ቆራጥነት ሃያል የሆኑትን የቅኝ ገዥ ኃይሎች እንኳን ሳይቀር ድል ማድረግ እንደሚያስችል ያረጋገጠ ነው።
የዓድዋ ገድል ዛሬም እንፀባራቂነቱ እንደቀጠለ ነው።
አፍሪካውያነ የአንድነትን ጥቅም ከዓድዋ ድል በመገንዘብ፡ በምጣኔ ሀብታዊ፣ በፖለቲካዊ እና በባህላዊ መስኮች ያላቸውን ህብረት አጠናክረው ቀጥለዋል።
በአህጉሩ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መቆም እና ራስን መቻል ቁልፍ መፍትሄዎች እንደሆኑ ለማሳያነትም ያገለግላል።
በታምራት ቢሻው