የዕድገት መሰላል

You are currently viewing የዕድገት መሰላል

የሀገራት ከፍታ የሚፀናው በህብረተሰብ የጋራ ተሳትፎ ነው

እንደ ስሙ ታላቅ ነው፡፡ ታላቁ የቻይና ግንብ፡፡ ይህ! ታሪካዊ ግንብ የቻይና ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ የብልሃትና የጽናት፣  የአብሮነትና የድል አድራጊነት ማሳያ ነው። የዓለማችን ውበት ከሰው ልጆች ህብረት የመነጨ እንደሆነም አንዱ ማሳያ ነው! በማለት ያሞካሹታል የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን፡፡

በርግጥም ዓለም ወዝና ለዛዋ የሚያምረው በህዝቦች ፈገግታ ውስጥ ነው፡፡ ሰዎች ለበጎነት ተሰባስበው ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን አስበው ሲሰሩ ተአምር መፍጠር ይችላሉ፡፡ ቋጥኝን ፈንቅለው ሀገርን ያጥራሉ፡፡ እንደ ፈረስ የሚጋልበውን ወንዝ ገድበው አሳ ያስግራሉ፡፡

አዎ! ሰዎች በበጎነት ሲሰለፉ ከጭድ ውስጥ እሾህን፣ ከአለት ደግሞ ውሃን ያወጣሉ፡፡ ታሪክ የሚቀይር ዕውቀት፣ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ የሚያሾልክ ብልሃት እና ተራራን የሚደረምስ ጉልበት በሕዝብ ውስጥ አለ፡፡ ይህን እውነት እሩቅ ሳንሄድ በኢትዮጵያ ምድር  ከጀጎል እስከ ፋሲል ግንብ፣ ከላልይበላ  እስከ ሀላላ ኬላ…መመልከት እንችላለን፡፡

“ነገር በምሳሌ…” እንዲል የሀገሬ ሰው በአንድ ወቅት ንዋይ ደበበ፣ አረጋሃኝ ወራሽ እና ፀጋዬ እሸቱ “ሁሉም ቢተባባር”  በማለት ተባብረው ከዘፈኑት  ዘመን አይሽሬ ስራቸው ጥቂት ስንኞችን ተውሰን የጨዋታችንን ጣምና እንጨምር፡፡

“ቢሰራ ቢደክም ሁሉም ሰው ቢተጋ፣

አምላክ ችሮን ነበር የተፈጥሮን ጸጋ”። አዎ!  ምድራችን ፀጋዋ የተትረፈረፈ ነው። ዋናው ነገር የሰዎች ህብረትና ትጋት ነው። ለዚህ ደግሞ በዓለም ዙሪያ አያሌ አብነቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ የቻይና ግንብ ፕላኔቷ ቅርሴን ልቁጠር፣ ውበቴን ልዘርዝር ካለች አንድ የምትለው ነው። የዓለም ቅርሱ የቻይና መገለጫ አጠቃላይ ርዝመቱ ከ21 ሺህ ኪሎ ሜትር  በላይ ነው፡፡ በቻይናውያን ትብብር የተሰራው ይህ ቅርስ  በህዝብ ተሰርቶ በህዝብ እየተጠበቀ፣ እየተደነቀም ከ 2000 ዓመታት በላይ ዕድሜን  አስቆጥሯል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ1987 ታላቁ ግንብ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) መረጃ እንደሚጠቁመው ይህ ግንብ በትላንትና በዛሬ መካከል የቆመ የቻይና ስልጣኔ መስታወት ነው፡፡ በየዓመቱም ከመላው ዓለም የተውጣጡ 50 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ይጎበኙታል፡፡

 ቻይናውያን ይህንን ታላቅ ግንብ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያቸውንም ሆነ አጠቃላይ ማንነታቸውን ዝንፍ በማይል የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ስነ ልቦናዊ አጥር መገንባት የቻሉት በህብረታቸው እንደሆነ አሜሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኔልሰን ዋልድሮን “ታላቁ የቻይና ግንብ” በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 27 ቀን 1990 ባሳተሙት ጥናታዊ መፅሀፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከቻይና አለፍ ስንል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ በደቡብ ኮሪያ የተጀመረው  የሳኢማኡል ኡንዶንግ ወይም የአዲስ መንደር ንቅናቄ፣ የህብረተሰብ ተሳትፌ ምን ያህል ሀይል እንዳለው አንዱ ማሳያ ነው። ይህ ንቅናቄ በሀገሪቱ  የገጠር መሠረተ ልማትን በማሻሻል እና የማህበረሰብ ልማትን በማስፋፋት ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡ መንገዶችን፣ ድልድዮችን እና የግብርና መሠረተ ልማቶችን ለማሻሻል የገጠሩ ክፍል ነዋሪዎች በፈቃደኝነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል።

ንቅናቄው ራስን መቻልን፣ ታታሪነትን እና ትብብርን  በማህበረሰቡ ልቦና አበክሮ ማስረፅ ያስቻለ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በደቡብ ኮሪያ በከተሞች እና በገጠር ልማት መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ረገድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ በደቡብ ኮሪያ ዮንሴን ዩኒቨርሲቲ  ሚሬ ካምፓስ  መምህርና ተመራማሪ ሱንግጆ ኪም (ዶ/ር) በኮሪያ ዓለም አቀፍ የምርምር መፅሔት(International Journal of Korean History) ላይ ባሳተሙት ስራቸው ገልፀውታል፡፡

ባህላዊ የጃፓን ቤቶች ደግሞ የማህበረሰብ ተሳትፎ ምን ያህል ሀይል እንዳለው ምስክር ሆነው በዓለም ታሪክ ላይ በደማቁ ሰፍረዋል፡፡ መንደሮቹ የተገነቡት  በአካባቢው ባሉ የእንጨት ሰራ ባለሙያዎች በጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡ እነዚህ መንደሮች በጃፓን ስልጣኔ ውስጥ የአብሮነትና የከፍታ መለኪያ ናቸው፡፡

እንደ ኪዮቶ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ በእንጨት ውጤቶች ብቻ በሚባል ደረጃ የተገነቡት መንደሮች  አካባቢዎቹን ከዘመናዊ ኑሮ  ጋር ያዋሀዱ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል መኖሪያ፣ በሌላ በኩል መነገጃ፣ የሀር ትል ማርቢያዎች እና ለጃፓን ጨርቃጨርቅ ኢንደስትሪ የግበአት ማቅረቢያዎች በመሆን ለዘመናት ያገለገሉት እነዚህ መንደሮች ልክ እንደ ኢትዮጵያ “እድገት በህብረት” በሚባል ዘመቻ አይነት በበጎ ፈቃደኞች የተገነቡ ናቸው፡፡

ጃፓን የህብረተሰብ ተሳትፎን ምን ያህል ኢኮኖሚዋን፣ ማህበራዊ መስተጋብሯን እና ሁለንተናዊ ከፍታዋን በፅኑ መሰረት ላይ እንደገነባችበት በአውስትራሊያ ሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የጃፓን ጥናት ፕሮፌሰር አኪሂሮ ኦጋዋ እና   የዘመናዊቷ ጃፓን ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሲሞን አቬኔል እ.ኤ.አ 2023 ʼHandbook of Civil Society in Japanʼ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ መፅሀፍ ላይ ሰፍሯል፡፡

ፊታችንን ወደ አፍሪካ ስንመልስ  ሩዋንዳን እናገኛለን፡፡ “ኡሙጋንዳ”  የተሰኘው የማህበረሰብ ተሳትፎ በአፍሪካ ምድር ለተምሳሌትነት የሚቀርብ የበጎነት፣ አብሮነትና ድል አድራጊነት መገለጫ ነው፡፡  ይህ ወርሃዊ የማህበረሰብ ተሳትፎ ሩዋንዳን ፅዱና ማራኪ አድርጓታል፡፡

ዛሬ ሩዋንዳ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎቿን በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተንከባከበች የአፍሪካ ሀገራት የፅዳት ተምሳሌት ሆናለች፡፡  በህብረተሰብ ተሳትፎ የለሙ አረንጓዴ ስፍራዎቿ፣ ንፁህ መንገዶቿ እና ቀልብን የሚገዙት የመናፈሻ ስፍራዎቿ  እንደ ሀገር ለውጥ ለማምጣት በጋራ ዓላማ መሰባሰብን መርህ ያደረገው የ”ኡሙጋንዳ” ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህ ንቅናቄ እ.ኤ.አ በ1962 ከነጻነት በኋላ የተፈጠረ ማህበራዊ አደረጃጀት  ነው፡፡  ቀደም ሲል ʼኡሙቢዚʼ ተብሎ ይጠራ ነበር፣ ትርጉሙም ‘እርስ በርስ ለመረዳዳት የተለየ ቀን’ እንደማለት ነው።

ይህ መርሃ ግብር ወር በገባ የመጨረሻው ቅዳሜ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ይከናወናል። በፅዳት፣ በልዩ ልዩ ልማቶች እና በጋራ ፈገግታ እየደመቀ ቢያንስ ለሦስት ሰዓታት ይቆያል፡፡ ይህ ንቅናቄ እ.ኤ.አ. በ1994 በተከሰተው ዘግናኝ የእርስ በእርስ እልቂት የተዛባ ቢሆንም ከ1998 ጀምሮ ሩዋንዳን እንደገና ለመገንባት በተደረገው ጥረት እና ይህንን ተከትሎ እየተመዘገበ ባለው ዕድገት ውስጥ ግሩም ለውጥ ማምጣቱን የሩዋንዳ አስተዳደር ቦርድ ʼRwanda Governance Boardʼ  “Impact Assessment of Umuganda ከ2007 እስከ 2016 ” በሚል ርዕስ  ባደረገው ጥናትዊ ሰነድ ላይ ሰፍሯል፡፡

ዋና መቀመጫውን በሀገረ እንግሊዝ ያደረገው  እና እ.ኤ.አ ጥቅምት 1974 በይፋ የተመሰረተው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፋውንዴሽን (CAF) እ.ኤ.አ 2024 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በዓለማችን የህብረተሰብ ተሳትፎን አሊያም የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ባህል በማድረግ ኢንዶኔዥያ፣ ኬንያ፣ ሲንጋፖር፣ ዩክሬን እና ዩናይትድ ስቴት ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። እ.ኤ.አ በ2023 በዓለማችን 4 ነጥብ 3 ቢልዮን የሚሆኑ ዜጎች ቢያንስ በአንድ ጉዳይ ላይ በበጎ አድራጎት ስራ ተሳትፈዋል፣ ይላል መረጃው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ በ2012 ዓመተ ምህረት  የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማብሰሪያ መርሃ ግብር በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ መከናወኑ ይታወሳል፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት መርሃ ግብሩ ሀገራዊ አንድነት፣ ማህበረሰባዊ ትስስር ማሻሻልና ሀገራዊ ሰላም ለማምጣት ሚናው ከፍተኛ ነው። ወጣቶቹ በቆይታቸው የህይወት ተሞክሮ የሚያገኙበትና የሀገራቸውን አካባቢ የሚያውቁበት መሆኑን ጠቅሰው ራስን ከመንከባከብ ይልቅ ለሌሎች ዕውቀትንና ሀብትን ማካፈል፣ ራሳቸውን ሰውተው ሀገር እንዳቆዩ ጀግኖች ሁሉ በጎ ስራም ጀግንነት ነው!  ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በርግጥም ከላይ የገለፅናቸው የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት የሀገራት ከፍታ የሚለካውና የሚፀናው በህብረተሰብ በጎነትና የጋራ ተሳትፎ ነው፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review