ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን ያገኙት በስተርጅና ዘመናቸው ነበር፡፡ ከመሸ ያገኙትን አንድዬ ልጃቸውን እንዲሰው ህልም ይታያቸዋል። ለልጃቸውም ‘በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ’ አሉት። ልጃቸው እስማኤልም፣ ‘አባቴ ሆይ የታዘዝከውን ፈፅም!’ በማለት ትዕዛዙን ለመቀበል ፈቃደኝነቱን አሳየ∫ ሲሉ የእስልምና ሃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ አብዱልመናን ሁሴን ያስረዳሉ፡፡
ነብዩ ኢብራሂም ነብይ ቢሆኑም ሰውም ናቸው። ልጅን ያህል ነገር ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት ከባድ ፈተና ቢሆንም፤ ከፈጣሪ ትእዛዝ አይበልጥም ብለው ለመፈፀም ሲዘጋጁ ከሰማይ በግ መጥቶላቸው በልጃቸው ምትክ በጉን አረዱ፡፡ በኢድ አል አድሃም እርድ ይፈፀማል፡፡ ይህም ነብዩ ኢብራሂምን መነሻ በማድረግ የሚከናወን ነው፡፡ የሀጂ ሥነ ስርዓት ማካሄድ፣ አላህን ማመስገን፣ እርድ መፈፀም እንዲሁም ከቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ጋር በደስታ ማሳለፍ ሌሎች ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሆኑ ሼህ አብዱልመናን ያነሳሉ፡፡
ነብዩ በስተርጅና ያገኙትን የበኩር ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ ታዛዥነትና ፅናት ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡ ለፈጣሪ መታዘዝ ውጤት ያመጣል፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ፈተናውን በመወጣታቸውና በመታዘዛቸው በልጃቸው ምትክ በግ መጥቶላቸው አርደዋል፡፡ አሁን ዓለም ላይ የሚታየው የሰላም እጦት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውሱ የፈጣሪን ትዕዛዝ ካለማክበርና የመታዘዝ እሴት መሸርሸር ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ሼህ አብዱልመናን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያም የተለያየ እምነት፣ ቋንቋ፣ ፍላጎት… ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጋምደው የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ የአብሮነት እሴቶች እየተሸረሸሩ በመምጣታቸውና የሀሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ አካሄድ የሚፈቱበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ ሰላምና አለመረጋጋት እያጋጠመ ሀገርን ወደኋላ ሲጎትቱ ቆይተዋል፡፡ “ስለሰላም አስፈላጊነት ለኢትዮጵያውያን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡ የሰላም እጦትን ከማንም በላይ ያውቁታል፡፡” የሚሉት ሼህ አብዱልመናን፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ታዛዥነትን፣ መከባበርን፣ መደማመጥን መለማመድ ይገባናል ብለዋል፡፡
የተለያዩ ፍላጎቶችን አጣጥሞ ለመሄድ፣ ህዝቦቿ ተከባብረው፣ በወንድማማችነትና እህትማማችነት መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል መስራት ይገባል፡፡ ይህንን መፍጠር ከተቻለ የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ ትኩረት ድህነት ላይ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ምክክሩ ፍሬያማ እንዲሆን ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ፣ የሚገኘውን ግብዓትም ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንዳለበት ሼህ አብዱልመናን ያስገነዝባሉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በተከበረበት ወቅት ያስተላለፉት መልእክትም የበዓሉ አንድምታ እየተካሄደ ላለው የምክክር ሂደት ብዙ የሚያስጨብጠው ቁም ነገር እንዳለ ያመለክታል፡፡
“በኢትዮጵያ ሳይፈቱ ሲንከባለሉ የመጡና በዘመናችን የተፈጠሩ አሁናዊ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ሀገርን ለማዳን፣ የህዝብን ጥቅም ለማስከበር፣ ከዛሬ የተሻለ ነገን ለመፍጠር ልክ እንደ ነብዩ ኢብራሂም ብዙ ነገሮችን መስዋዕት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠርም ነፍጥን መጣልና የራስን ዋሻ ትቶ ወደ መስክ መውጣትን፣ ምቾትንና ፍላጎትን መተው ይፈልጋል። ከመቀበል በላይ መስጠትን ይሻል፡፡ እንደ ኢብራሂም በጣም የምንሳሳለትን ነገር ለመሠዋት መቁረጥ ይፈልጋል። ሁላችንም ለመሥዋዕትነት ከተዘጋጀን የማይሳካ የሰላም መንገድ የለም፡፡” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ “ምክክር የሚሳካው የተሻለ ሐሳብና የላቀ እውቀት በማዋጣት ብቻ አይደለም። ሌላ ወሳኝ ነገር ይፈልጋል፡፡ እርሱም መስዋዕትነት ነው፡፡ የራስን ፍላጎት መሰዋት መቻል አለብን፡፡ ለትልቅ ግብ ሲባል ይቅርብኝ ማለት አለብን፡፡ ከእኔ የተሻለ ሐሳብና ልምድ፣ እውቀትና ጥበብ ሊኖር ይችላል ብለን ማመንና መቀበል አለብን፡፡ ለተሻላ መገዛት አለብን፡፡ እንደ ኢብራሂም ያሳደግናቸውን ብቻ ሳይሆን አብረውን ያደጉትን ብዙ ጠባዮች ለመሰዋት መዘጋጀትን ይጠይቃል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊና አካታች እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በሂደቱ ሁሉም አካላት በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደኋላ የሚቀር ወገን እንዳይኖር ጊዜ በመስጠት በሩን ክፍት በማድረግ እንዲሳተፉ እያደረገ ነው፡፡ እስከአሁን ባለው ሂደትም ለቀረበው የምክክር ጥሪ ከህዝብ በጎ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
“በምክክር እንደሀገር ያሉ የአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በጋራ በመለየትና በመመካከር ሀገርን ማሻገር ይቻላል በሚለው ላይ እምነት ከማሳደር ይጀምራል” የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ ምክክር አዋጪው መንገድ ነው የሚለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑ በሚያመቻቸው የምክክር መድረኮች ላይ ተሳታፊዎች ሲንከባለሉ ለመጡና አሁናዊ ችግሮች መነሻ ምክንያቶች ናቸው የሚሏቸውን አጀንዳዎች ያለምንም ስጋት በነፃነት ሲሰጡ እየታየ ነው፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና አመለካከቶች፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግርና ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩ እነዚህን በመሻገር በሂደቱ እምነት በመያዝ በቁርጠኝነት አሉ የሚባሉ ችግሮችን እያነሱ ይገኛሉ፡፡
ምክክር በባህሪው ሙሉ ፈቃደኝነትና ትብብርን የሚጠይቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፣ ህዝብን የሚወክሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሂደቱ ላይ እምነት እየጣሉ መምጣታቸው ለምክክሩ ስኬት ወሳኝነት አለው፡፡ ከዚህ ባሻገር ለምክክሩ ስኬታማነት ምክክር ምን ይፈልጋል? የሚለውንም መረዳት ወሳኝ እንደሆነ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ያነሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሀሳብ ልዩነት፣ አለመግባባት፣ ግጭት አልፎ ተርፎ የህይወት መጥፋት በሚያጋጥምበት ወቅት ሰላምና እርቅ የሚወርድባቸው የቆዩ ባህልና እሴቶች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ባህሎች ጎልብተው ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ባለመደረጉ፣ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ እልህ መጋባት፣ ግጭትንና ጦርነትን አማራጭ በማድረግ ሀገር ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች፡፡
ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ልንተዋቸው የሚገቡ በጎ ያልሆኑ ልማዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ አለመደማመጥ እንደሆነ አቶ ጥበቡ ያነሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በፖለቲካው መድረክ ከመደማመጥ ይልቅ መናገር፣ ሀሳብን በሀይል ሌላው ላይ ለመጫን የመፈለግ ጉዳይ ይታያል፡፡ ይህ ባህል ሊቀረፍ የሚገባውና ከምክክር ጋር አብሮ የማይሄድ ጠባይ ነው፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) የፌዴራል ተቋማት አጀንዳ የማሰባሰብ መክፈቻ ስነ ስርዓት ወቅት የተናገሩት ንግግርም ይህንን ያጠናክራል፡፡ “ለረጅም ዘመን ፖለቲካችን የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ አልነበረም፡፡ በምክክር ሂደት ፖለቲካችን የተለያዩ ህዝቦችን ፍላጎቶች፣ ብዝሃነቶችን የሚያዳምጥ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል” ነው ያሉት፡፡
አለመከባበር ሌላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታይ በጎ ያልሆነ ባህል እንደሆነ አቶ ጥበቡ ያነሳሉ፡፡ ተከባብሮ መነጋገር ካልተቻለ ትርጉም ወዳለው መግባባት መምጣት ያስቸግራል። አንዱን ዝቅ ሌላውን ከፍ ማድረግ፣ ‘እኔ የተሻልኩ ነኝ’፤ ‘እበልጣለሁ’ አይነት አካሄድ፤ አንዱን ጉዳይ በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ ያለመመልከት፣ ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን ያለማየት በፖለቲካው ዘንድ ይታያል፡፡ በአብዛኛው የብቻ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እንጂ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን መካከለኛ መንገድ ይዞ የመሄድ ነገር አይታይም። እነዚህ ልማዶችና ጠባዮች ከምክክር ጋር የሚሄዱ ባለመሆኑ፤ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን ምክክርና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርጉ መንገዶችን ማየት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ቀጣይስ ምን ይጠበቃል?
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እስከ አሁን ከ11 ክልሎች እና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች በድምሩ ከ1 ሺህ 234 ወረዳች ወኪሎች ተለይተው አጀንዳ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም 126 ሺህ 22 የወረዳ ተወካዮች በሂደቱ ተሳትፈዋል። ቀጣይ ከትግራይ ክልልና ዳያስፖራው ማህበረሰብ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ይቀራሉ፡፡
በሀገራችን ታሪክ በሀገሩ ዕጣ ፈንታ ህብረተሰቡ ብዙም ተሳትፎ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ በምክክሩ ሂደት ህብረተሰቡ የሚሳተፍበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አካታች የሆነ ምክክር እንዲሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በንቃት እየተሳተፉ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በምክክሩ ሂደት የማይሳተፉ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነፍጥ ያነገቡና ሌሎችም አካላት ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በምክክሩ ሂደት የአጀንዳ ማሰባሰቡን ለማጠናቀቅ የተወሰኑ ስራዎች ይቀራሉ። የአጀንዳ ማሰባሰቡ ከተጠናቀቀ በኋላም አጀንዳዎች ተቀርፀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ይካሄዳል፡፡ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በአንድ ጊዜ መፍታት አይቻልም፤ መሰረታዊ የሆኑ የአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮች ከተፈቱ ሌሎችም በሂደት እየተፈቱ ይሄዳሉ፡፡ ቀጣይ ትውልድም እየፈታቸው የሚሄድበት እድል እንደሚፈጠርም አቶ ጥበቡ ጠቁመዋል።
ሼህ አብዱልመናን እንደሚሉት፣ “ሀገር ተመካከሩ!” እያለች የምታቀርበውን ጥሪም ህዝቡ በአግባቡ ተረድቶ ምክክሩ ፍሬያማ እንዲሆን፣ የሚገኘውን ግብአት ወደ ተግባር እንዲቀየር የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት፡፡ በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች የነበሩ ዕድሎች ነበሩ፤ አምልጠውናል፡፡ አሁን ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመመካከር ችግሮችን ለመፍታት የመጣውን ዕድል መጠቀም ይገባል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በፌዴራል ደረጃ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ በተናገሩት ሀሳብ ጹሑፋችንን እንቋጨው።
“የምክክሩ ሂደት እንዲሳካ ማድረግ የምንችለው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን። በዚህ ሂደት ማንም ተመልካች ማንም ታዛቢ የለም፡፡ ባለቤት ነን የምንል ከሆነ ያለንን እውቀት፣ ጊዜና ጥበብ በሂደቱ ላይ ማዋል አለብን፡፡ የሚያጣሉንና የሚከፋፍሉን አካላት ወይም ቡድኖች ድምፅ የሚሰማው በጣም ትክክል ስለሆኑ አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን (the Silent majoriry) ዝምታን ስለመረጥን ነው፡፡”
በስንታየሁ ምትኩ