በዉይይቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ለአራት ዓመታት የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተና ስርዓት እንዲይዝ እና ተማሪዎች የለፉበትን ውጤት እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት ውስጥ መከላከያ ሠራዊት እና ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ከፈተና ስርቆትና ኩረጃ በመውጣት አጥንቼ አውቄ ፈተናውን ማለፍ አለብኝ የሚል አስተሳሰብ ያለው ምክንያታዊ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸዉ ቀደም ባሉት ጊዜያት በስርቆትና በኩረጃ ይታወቅ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ስርዓት እንዲይዝ መንግስት በወሰደው ቁርጠኝነት የፖሊስ ለውጥ በማድረግ አሁን ላይ ተማሪዎች ስርዓት ይዘው በመፈተን ላይ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡
ተማሪዎች ስርዓት ይዘው በመፈተን ያጠኑትን፣ ያነበቡትንና የለፉበትን ውጤት እንዲያገኙ ከማስቻልም በላይ በዩኒቨርስቲዎች በተመሳሳይ ሰዎች ለፍተው ጥረው አንብበው የሚበቁበት ሀገር የሚገነባበት ሥርዓት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ጄይላን አብዲ ለአዲስ ሚዲያኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንዳስታወቁት የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ በጋራ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ