የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ (Mpox) “ክሌድ 1” እና “ክሌድ 1ቢ” በሚባሉ በሁለት ዋነኛ የቫይረስ ዝርያዎች አማካይነት ሲሠራጭ ቆይቷል።
“ክሌድ 1” የሚባለው የቫይረሱ ዓይነት በማዕከላዊ አፍሪካ በስፋት የሚገኝ ሲሆን፣ “ክሌድ 1ቢ” የተባለው ደግሞ ከ“ክሌድ 1” ኋላ እየተስፋፋ ያለ እና በጣም አደገኛ መሆኑ ይነገራል።
በፈረንጆቹ 2022 ቀለል ያለው እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው “ክሌድ 2” የተባለው የበሽታው ዝርያ በዓለም ዙሪያ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በወቅቱ በሽታው ቫይረሱ ተከስቶባቸው የማያውቁት የአውሮፓ እና የእስያ ሀገራትን ጨምሮ አንድ መቶ በሚጠጉ ሀገራት ውስጥ ተከስቶ ነገር ግን ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በመከተብ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የበሽታው ምልክቶች

በዝንጀሮ ፈንጣጣ በተያዘ ሰው ላይ መጀመሪያ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ ጀርባ ህመም እና የጡንቻ ህመምን ያካትታል።
ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ ሽፍታ የሚከሰት ሲሆን፣ በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫ ላይ ይከሰታል።
በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም ይከስማል።
ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
በሽታው በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በራሱ የሚጠፋ ይሆናል።
በበሽታው የተያዘው ሰው በጣም የተጎዳ ከሆነ፣ ቁስለቱ አጠቃላይ ሰውነቱን፣ በተለይ አፍ፣ ዓይን እና የመራቢያ አካላት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
የበሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፊያ መንገድ
በሽታው ቤተ ሙከራ ውስጥ በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ ቫይረስ ሲሆን፣ በሰውነት ንክኪ ይተላለፋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወሲባዊ ግንኙነትን፣ የቆዳ ንክኪን እና በትንፋሽ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።

የበሽታው ቫይረስ ወደ ሰውነት በቆሰለ ቆዳ፣ በመተንፈሻ አካላት፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ሊገባ ይችላል።
በቫይረሱ የተበከሉ የመኝታ አልባሳት፣ በልብሶች እና በፎጣዎች አማካይነት በሚኖር ንክኪም በሽታው ሊተላለፍ ይችላል።
ቫይረሱ ካለባቸው ዝንጀሮ እና አይጦችን ከመሳሳሉ ጋር የሚኖር ንክኪም ሌላኛው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዓለም ዙሪያ በበርካታ ሀገራት ውስጥ በተከሰተበት ጊዜ ቫይረሱ በዋናነት በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ አማካይነት ነበር የተሠራጨው።
ባለፈው ዓመትም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የበሽታው ወረርሽኝ የተስፋፋው በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ቫይረስ ሊገኝ መቻሉ ተጠቁሟል።
መከላከያ እና ህክምናው
የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለማከም የተዘጋጀ ህክምና፣ የታመሙ ሰዎችን ለማዳን በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፣ ነገር ግን ህክምናው ምን ያክል ውጤታማ እንደሆነ የሚያሳይ ውስን ጥናት እንዳለ ነው የሚገለጸው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝን፣ በሽታውን በመከላከል መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን፣ ይህንንም ለማድረግ ተመራጩ መንገድ የመከላከያ ክትባት መስጠት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ሦስት በሽታውን መከላከያ የክትባት ዓይነቶች ቢኖሩም፣ ክትባቶቹ የሚሰጡት ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ላላቸው ብቻ ነው።
ይሁንና ያሉት የክትባት ዓይነቶች አዲስ ከተከሰተው የበሽታው ዝርያ አንፃር ምን ያክል የመከላከል አቅም አላቸው የሚለውን ለማወቅ ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረግ ስለሚያስፈልግ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ሰው መከተብ አለበት ብሎ እንደማይመክር ተገልጿል።
ባለፈው ዓመትም የአፍሪካ ህብረት ለኮቪድ ተመድቦ ከነበረ ገንዘብ ላይ 10.4 ሚሊየን ዶላር ለሲዲሲ በመስጠት የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት መደገፉን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
የአፍሪካ ሲዲሲ እንደሚለው ካለፈው ዓመት ጥር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ ከ14 ሺህ 500 በላይ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከ450 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው አልፏል።
የበሽታው ክስተት 96 በመቶው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተመዘገበ ሲሆን፣ ጎረቤት ወደሆኑት እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ እምብዛም ወደ ማይታወቅባቸው ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ተስፋፍቶ እንደነበርም ይታወሳል።
በታምራት ቢሻው