AMN-ኅዳር 5/2017 ዓ.ም
የደቡብ ሱዳን ልዑካን ቡድን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅት የተከናወኑ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራትን ጎብኝተዋል።
ልዑካን ቡድኑ ከደቡብ ሱዳን የስርዓተ ፆታ፣ ህፃናትና ማህበራዊ ደህንነት እና ከግብርና ሚኒስቴር የተውጣጣ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት በተለይም ሴቶችና ህፃናት ግንባር ቀደም ተጎጂ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህንኑ ከግምት በማስገባት መንግስት ዜጎችን በማህበራዊ ጥበቃ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ በተገኘ የበጀት ድጋፍ የከተማና የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔትና ሥራ ፕሮጀክት ነድፎ እየተገበረ መሆኑንም አመልክተዋል።
በተለይ በተለያየ ምክንያት ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉና ልጆቻቸውን የያዙ እናቶችን ከጎዳና በማንሳት መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ ለአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን ልዑካን ቡድን በመሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅት የምግብ፣ የመጠለያ፣ የስነ ልቦና፣ የህይወት ክህሎትና አጫጭር የሙያ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አስተማሪ ናቸው ብለዋል።
ድርጅቱ የህፃናትን መብትና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በህፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ ህፃናት እየተሰጠ ያለው የተቀናጀ አገልግሎትም የሚበረታታና ጠቃሚ ልምድ መሆኑን መግለጻቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።